መሳፍንት 15 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምሳምሶን ፍልስጥኤማውያንን ተበቀለ 1 ከጥቂት ጊዜ በኋላ በስንዴ መከር ወራት ሳምሶን አንድ የፍየል ጠቦት ይዞ ሚስቱን ለማየት ሄደ፤ እርሱም፣ “ሚስቴ ወዳለችበት ጫጕላው ቤት ልግባ” አለ፤ አባቷ ግን እንዲገባ አልፈቀደለትም። 2 አባትየውም፣ “ፈጽሞ የጠላሃት መሆንህን ስለ ተረዳሁ ለሚዜህ ድሬለታለሁ፤ ታናሽ እኅቷ ከርሷ ይልቅ ውብ አይደለችምን? እርሷን አግባት” አለው። 3 ሳምሶንም መልሶ፣ “ከእንግዲህ በፍልስጥኤማውያን ላይ በሚደርሰው ጕዳት ተጠያቂ አልሆንም” አላቸው። 4 ከዚያም ወጥቶ በመሄድ ሦስት መቶ ቀበሮች ያዘ፤ የሁለት ሁለቱን ጭራ አንድ ላይ ካሰረ በኋላ ችቦ ወስዶ ጥንድ ሆኖ ከተያያዘው ጭራ ጋራ አሰረው። 5 ችቦውን በእሳት አቀጣጥሎ ቀበሮቹን በፍልስጥኤማውያን የእህል አዝመራ ላይ ለቀቃቸው፤ ነዶውንና የቆመውን አዝመራ እንዲሁም የወይኑንና የወይራውን ተክል አቃጠለ። 6 ፍልስጥኤማውያን፣ “ይህን ያደረገው ማን ነው?” ብለው ሲጠይቁ፣ “ሚስቱ ለሚዜው ስለ ተሰጠችበት የተምናዊው ዐማች ሳምሶን ነው” የሚል መልስ አገኙ። ስለዚህም ፍልስጥኤማውያን ወጥተው ሴቲቱንና አባቷን በእሳት አቃጥለው ገደሏቸው። 7 ሳምሶንም፣ “እንግዲህ እናንተ ይህን ካደረጋችሁ እኔ ደግሞ ሳልበቀላችሁ አልመለስም” አለ። 8 ክፉኛ መታቸው፤ ከእነርሱም ብዙዎችን ገደለ፤ ከዚያም ወርዶ በኤጣም ዐለት ዋሻ ተቀመጠ። 9 ፍልስጥኤማውያን ወጥተው በይሁዳ ሰፈሩ፤ ከዚያም በሌሒ አጠገብ ተበታትነው አደፈጡ። 10 የይሁዳም ሰዎች፣ “ልትወጉን የመጣችሁት ለምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቋቸው። እነርሱም “እኛ የመጣነው ሳምሶንን ልናስርና ያደረገብንን ልናደርግበት ነው” ብለው መለሱላቸው። 11 ከዚያም ሦስት ሺሕ ሰዎች ከይሁዳ ተነሥተው በኤጣም ዐለት ወዳለው ዋሻ ወርደው ሳምሶንን፣ “ፍልስጥኤማውያን ገዦቻችን መሆናቸውን አታውቅምን? ያደረግህብንስ ነገር ምንድን ነው?” ብለው ጠየቁት። ሳምሶንም፣ “ያደረግሁት እነርሱ ያደረጉብኝን ነው” በማለት መለሰላቸው። 12 እነርሱም፣ “አስረን ለፍልስጥኤማውያን ልንሰጥህ ይኸው መጥተናል” አሉት። ሳምሶንም፣ “እናንተ ራሳችሁ ላትገድሉኝ ማሉልኝ” አላቸው። 13 እነርሱም፣ “አስረን ብቻ ለእነርሱ አሳልፈን እንሰጥሃለን እንጂ ራሳችን አንገድልህም” አሉት፤ ከዚያ በሁለት አዳዲስ ገመድ አስረው ከዐለቱ ዋሻ አወጡት። 14 ሳምሶን ሌሒ እንደ ደረሰም ፍልስጥኤማውያን እየጮኹ ወደ እርሱ መጡ፤ በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር መንፈስ በሳምሶን ላይ በኀይል ወረደበት። እጆቹ የታሰሩበትም ገመድ እሳት ውስጥ እንደ ገባ የተልባ እግር ፈትል ሆኖ ከእጆቹ ላይ ወደቀ። 15 ከዚያም በቅርቡ የሞተ የአንድ የአህያ መንጋጋ አይቶ ከመሬት አነሣ፤ በዚያም አንድ ሺሕ ሰው ገደለ። 16 ሳምሶንም፣ “በአንድ የአህያ መንጋጋ፣ ሺሕ ሰው ዘራሪ፤ በአንድ የአህያ መንጋጋ፣ ሺሕ ሬሳ አነባባሪ” ብሎ ፎከረ። 17 ይህን ተናግሮ እንዳበቃ የአህያውን መንጋጋ ከእጁ ወዲያ ወረወረው፤ የዚያም ቦታ ስም ራማት ሌሒ ተብሎ ተጠራ። 18 እጅግ ተጠምቶ ስለ ነበር፤ “እነሆ፤ ለአገልጋይህ ይህን ታላቅ ድል አጐናጽፈሃል፤ ታዲያ አሁን በውሃ ጥም ልሙት? እንዴትስ በእነዚህ ባልተገረዙ ፍልስጥኤማውያን እጅ ልውደቅ?” በማለት ወደ እግዚአብሔር ጮኸ። 19 እግዚአብሔርም በሌሒ ዐለት ሰነጠቀለት፤ ከዚያም ውሃ ወጣ፤ ሳምሶንም ያን ሲጠጣ በረታ፤ መንፈሱም ታደሰ። ስለዚህ ያ ምንጭ ዓይንሀቆሬ ተባለ፤ እስከ ዛሬም ድረስ በዚያው በሌሒ ይገኛል። 20 ሳምሶንም በፍልስጥኤማውያን ዘመን በእስራኤል ላይ ለሃያ ዓመት ፈራጅ ሆነ። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.