መሳፍንት 12 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምዮፍታሔና ኤፍሬም 1 የኤፍሬም ሰዎች ኀይላቸውን አሰባስበው ወደ ጻፎን በመሻገር ዮፍታሔን፣ “አሞናውያንን ለመውጋት ስትወጣ ዐብረንህ እንድንሄድ ያልጠራኸን ለምንድን ነው? ቤትህን በላይህ ላይ እናቃጥለዋለን አሉት።” 2 ዮፍታሔም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “እኔና ሕዝቤ ከአሞናውያን ጋራ ከፍተኛ ትግል ገጥመን በነበረበት ጊዜ ጠርቼያችሁ ከእጃቸው አላዳናችሁኝም፤ 3 እኔም እንደማትረዱኝ በተረዳሁ ጊዜ በሕይወቴ ቈርጬ አሞናውያንን ለመውጋት ተሻገርሁ፤ እግዚአብሔርም ድሉን ሰጠኝ። ታዲያ ዛሬ እኔን ለመውጋት የመጣችሁት ለምንድን ነው?” 4 ከዚያም ዮፍታሔ የገለዓድን ሰዎች አሰባስቦ ከኤፍሬም ጋራ ተዋጋ። ኤፍሬማውያን ገለዓዳውያንን፣ “እናንተ ገለዓዳውያን ከኤፍሬምና ከምናሴ የከዳችሁ ናችሁ” ይሏቸው ስለ ነበር በብርቱ መቷቸው። 5 ገለዓዳውያን ወደ ኤፍሬም የሚያሻግሩትን የዮርዳኖስን መልካዎች ያዙ። ታዲያ አምልጦ የሚሸሽ አንድ ኤፍሬማዊ ለመሻገር በሚጠይቃቸው ጊዜ፣ የገለዓድ ሰዎች “አንተ ኤፍሬማዊ ነህ?” ብለው ይጠይቁታል፤ ያም ሰው፣ “አይደለሁም” ብሎ ከመለሰላቸው፣ 6 እስኪ “ሺቦሌት” በል ይሉታል፤ ቃሉን በትክክል ማለት ሳይችል ቀርቶ “ሲቦሊት” ካለ፣ ይዘው እዚያው እመልካው ላይ ይገድሉታል። በዚያ ጊዜም አርባ ሁለት ሺሕ ኤፍሬማውያን ተገደሉ። 7 ዮፍታሔ በእስራኤል ላይ ለስድስት ዓመት ፈራጅ ሆነ። ገለዓዳዊው ዮፍታሔ ሞተ፤ ከገለዓድም ከተሞች በአንዲቱ ተቀበረ። ኢብጻን፣ ኤሎምና ዔብዶን 8 ከዮፍታሔ ቀጥሎ የቤተ ልሔሙ ኢብጻን በእስራኤል ላይ ፈራጅ ሆነ። 9 እርሱም ሠላሳ ወንዶችና ሠላሳ ሴቶች ልጆች ነበሩት። ሴቶች ልጆቹንም ከጐሣው ውጭ ለሆኑ ሰዎች ዳራቸው፤ ከጐሣው ውጭ የሆኑ ሠላሳ ልጃገረዶች አምጥቶ ከወንዶች ልጆቹ ጋራ አጋባቸው። ኢብጻን በእስራኤል ላይ ሰባት ዓመት ፈራጅ ሆነ። 10 ኢብጻን ሞተ፤ በቤተ ልሔምም ተቀበረ። 11 ከርሱም በኋላ ዛብሎናዊው ኤሎም በእስራኤል ላይ ዐሥር ዓመት ፈራጅ ሆነ። 12 ከዚያም ኤሎም ሞተ፤ በዛብሎን ምድር በኢያሎን ተቀበረ። 13 ከኤሎም ቀጥሎ የጲርዓቶናዊው የሂሌል ልጅ ዓብዶን በእስራኤል ፈራጅ ሆነ። 14 እርሱም በሰባ አህዮች ላይ የሚቀመጡ አርባ ወንዶች ልጆችና ሠላሳ ወንዶች የልጅ ልጆች ነበሩት፤ በእስራኤልም ላይ ስምንት ዓመት ፈራጅ ሆነ። 15 ከዚያም የሂሌል ልጅ ዓብዶን ሞተ፤ ኰረብታማ በሆነው በአማሌቃውያን አገር በኤፍሬም ምድር በጲርዓቶን ተቀበረ። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.