Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

መሳፍንት 11 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም

1 ገለዓዳዊው ዮፍታሔ ኀያል ጦረኛ ነበረ፤ አባቱ ገለዓድ ነበር፤ እናቱም ጋለሞታ ነበረች።

2 እንደዚሁም የገለዓድ ሚስት ለገለዓድ ወንዶች ልጆች ወለደችለት፤ እነርሱም ባደጉ ጊዜ ዮፍታሔን፣ “ከሌላ ሴት ስለ ተወለድህ ከቤተ ሰባችን ምንም ዐይነት ውርስ አይገባህም” በማለት አሳደዱት።

3 ስለዚህም ዮፍታሔ ከወንድሞቹ ሸሽቶ መኖሪያውን ጦብ በተባለች ምድር አደረገ፤ እዚያም ወሮበሎች ተሰባስበው ተከተሉት።

4 ከጥቂት ጊዜ በኋላም አሞናውያን በእስራኤል ላይ ጦርነት ባደረጉ ጊዜ፣

5 የገለዓድ አለቆች ዮፍታሔን ለማምጣት ወደ ጦብ ምድር ሄዱ።

6 እነርሱም ዮፍታሔን፣ “ከአሞናውያን ጋራ መዋጋት እንችል ዘንድ መጥተህ ምራን” አሉት።

7 ዮፍታሔም የገለዓድን ሽማግሌዎች፣ “ምነው ጠልታችሁኝ ከአባቴ ቤት አሳድዳችሁኝ አልነበረምን? ታዲያ አሁን ችግር ሲገጥማችሁ ነው የምትፈልጉኝ?” አላቸው።

8 የገለዓድ አለቆችም ዮፍታሔን፣ “እንግዲህ አሁን ወደ አንተ መጥተናል፤ አሞናውያንን እንድንወጋ በል ተነሥና ዐብረን እንሂድ፤ በገለዓድ በምንኖረው በሁላችንም ላይ አለቃ ትሆናለህ” አሉት።

9 ዮፍታሔም የገለዓድን ሽማግሌዎች፣ “አሞናውያንን ለመውጋት ወደ አገሬ ብትመልሱኝና እግዚአብሔር በእጄ አሳልፎ ቢሰጣቸው በርግጥ አለቃችሁ እሆናለሁ?” ሲል ጠየቃቸው።

10 የገለዓድ አለቆችም ዮፍታሔን፣ “እግዚአብሔር ምስክራችን ነው፤ ያልኸውንም በርግጥ እናደርጋለን” አሉት።

11 ስለዚህ ዮፍታሔ ከገለዓድ አለቆች ጋራ ሄደ፤ ሕዝቡም በላያቸው ላይ አለቃና አዛዥ አደረጉት፤ ዮፍታሔም የተናገረውን ቃል ሁሉ ምጽጳ ላይ በእግዚአብሔር ፊት ደገመው።

12 ከዚያም ዮፍታሔ ወደ አሞናውያን ንጉሥ፣ “ከእኔ ጋራ ምን ጠብ ቢኖርህ ነው መጥተህ አገሬን የወጋኸው?” በማለት መልእክተኞች ላከ።

13 የአሞናውያንም ንጉሥ ለዮፍታሔ መልእክተኞች፣ “ይህን ያደረግሁት እስራኤል ከግብጽ በወጣ ጊዜ በአርኖንና በያቦቅ ወንዞች መካከል ያለውንና እስከ ዮርዳኖስ ያለውን አገሬን ስለ ወሰዱብኝ ነው፤ አሁንም በሰላም መልሱልኝ” አላቸው።

14 ዮፍታሔም መልእክተኞቹን እንደ ገና ወደ አሞናውያን ንጉሥ ላካቸው፤

15 እንዲህም አላቸው፤ “ዮፍታሔ እንዲህ ይላል፤ እስራኤል የሞዓብንም ሆነ የአሞናውያንን ምድር አልወሰደም።

16 እስራኤል ከግብጽ በወጣ ጊዜ በምድረ በዳ አድርጎ ወደ ቀይ ባሕር ከዚያም ወደ ቃዴስ ሄደ።

17 እስራኤልም ወደ ኤዶም ንጉሥ፣ ‘በአገርህ እንዳልፍ እባክህ ፍቀድልኝ’ በማለት መልእክተኞችን ላከበት፤ የኤዶም ንጉሥ ግን አልሰማውም። ለሞዓብ ንጉሥም እንደዚሁ ላከበት፤ እርሱም አልተቀበለውም፤ ስለዚህ እስራኤል በቃዴስ ተቀመጠ።

18 “ቀጥሎም የኤዶምንና የሞዓብን ምድር በመዞር፣ በምድረ በዳው ተጕዞ ከሞዓብ በስተምሥራቅ በኩል በማለፍ ከአርኖን ማዶ ሰፈረ፤ የሞዓብም ድንበር አርኖን ስለ ነበር ወደ ሞዓብ ክልል አልገባም።

19 “ከዚያም እስራኤል በሐሴቦን ወዳለው ወደ አሞራውያን ንጉሥ ወደ ሴዎን መልእክተኞች ልኮ፣ ‘ወደ ገዛ ስፍራችን ለመሄድ በአገርህ እንዳልፍ ፍቀድልኝ’ አለው።

20 ሴዎን ግን በግዛቱ እንዲያልፍ ለመፍቀድ እስራኤልን አላመነውም፤ ሰራዊቱንም ሰብስቦ በያሀጽ ከሰፈረ በኋላ ከእስራኤል ጋራ ተዋጋ።

21 “ከዚያም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሴዎንንና ሕዝቡን ሁሉ በእስራኤል እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፤ አሸነፏቸውም። እስራኤልም በዚያ አገር የሚኖሩትን የአሞራውያንን ምድር በሙሉ ወረሰ፤

22 ከአርኖን እስከ ያቦቅ፣ ከምድረ በዳው እስከ ዮርዳኖስ ድረስ ያለውን የአሞራውያንን ድንበር በሙሉ ወረሱ።

23 “እንግዲህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር አሞራውያንን ከሕዝቡ ከእስራኤል ፊት አሳድዶ ካስወጣቸው፣ አንተ ለመውሰድ ምን መብት አለህ?

24 አምላክህ ካሞሽ የሰጠህን ይዞ ማቈየቱ ያንተ ፈንታ ነው፤ እኛም እንደዚሁ አምላካችን እግዚአብሔር የሰጠንን ሁሉ ርስት አድርገን እንወርሳለን።

25 አንተ ከሞዓብ ንጉሥ ከሴፎር ልጅ ከባላቅ ትበልጣለህን? ለመሆኑ እርሱ ከእስራኤል ጋራ ተጣልቷልን? ወይስ ተዋግቷልን?

26 እስራኤልም በሐሴቦንና በመንደሮቿ፣ በአሮዔርና በመንደሮቿ፣ በአርኖንም አቅራቢያ ባሉት ከተሞች ሁሉ ሦስት መቶ ዓመት ተቀምጦ በነበረበት በዚያ ጊዜ ስለ ምን አልወሰዳችኋቸውም ነበር?

27 እኔ አልበደልሁህም፤ አንተ ግን በእኔ ላይ ዘምተህ በድለኸኛል፤ እንግዲህማ ፈራጁ እግዚአብሔር በእስራኤላውያንና በአሞናውያን መካከል ዛሬ ይፍረድ።”

28 የአሞን ንጉሥ ግን ዮፍታሔ የላከውን መልእክት ከምንም አልቈጠረውም።

29 ከዚያም የእግዚአብሔር መንፈስ በዮፍታሔ ላይ ወረደ፤ ተነሥቶም ገለዓድንና ምናሴን አቋርጦ ሄደ። ገለዓድ ባለችው በምጽጳ በኩል አድርጎም በአሞናውያን ላይ ዘመተባቸው።

30 ዮፍታሔም እንዲህ ሲል ለእግዚአብሔር ተሳለ፤ “አሞናውያንን በእጄ አሳልፈህ ብትሰጠኝ፣

31 አሞናውያንን ድል አድርጌ በምመለስበት ጊዜ በመጀመሪያ ሊቀበለኝ ከቤቴ ደጅ የሚወጣው ማንኛውም ሰው ለእግዚአብሔር ይሆናል፤ እኔም የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጌ አቀርበዋለሁ።”

32 ከዚያም ዮፍታሔ አሞናውያንን ለመውጋት ወጣ፤ እግዚአብሔርም እርሱን በእጁ አሳልፎ ሰጠው።

33 ከአሮዔር አንሥቶ እስከ ሚኒት አካባ፣ ከዚያም ዐልፎ እስከ ክራሚም የሚገኙትን ሃያ ከተሞች ፈጽሞ አጠፋቸው፤ አሞናውያንም ለእስራኤል ተገዙ።

34 ዮፍታሔ ምጽጳ ወዳለው ቤቱ ተመለሰ። እነሆ፤ ልጁ አታሞ እየደለቀች በመዝፈን ልትቀበለው ወጣች፤ እርሷም አንዲት ልጁ ብቻ ነበረች፤ ከርሷ በቀር ወንድም ሆነ ሴት ልጅ አልነበረውም።

35 ባያትም ጊዜ ልብሱን በመቅደድ፣ “ወይኔ ልጄ ጕድ አደረግሽኝ! ጭንቅም ላይ ጣልሽኝ፤ ማስቀረት የማልችለውን ስእለት ለእግዚአብሔር ተስያለሁና” ብሎ በሐዘን ጮኸ።

36 እርሷም እንዲህ አለች፤ “አባቴ ሆይ፤ መቼም አንዴ ለእግዚአብሔር ቃል ገብተሃል፤ ጠላቶችህን አሞናውያንን አሁን እግዚአብሔር ተበቅሎልሃልና ቃል የገባኸውን ፈጽምብኝ።

37 ነገር ግን አንድ ነገር ብቻ እንድትፈቅድልኝ እለምንሃለሁ፤ ከእንግዲህ ባል ስለማላገባ ከባልንጀሮቼ ጋራ ወደ ተራሮች ወጥቼ እየዞርሁ ሁለት ወር እንዳለቅስ አሰናብተኝ።”

38 እርሱም፣ “በይ ሂጂ” ብሎ ለሁለት ወር አሰናበታት፤ እርሷም ከእንግዲህ ባል ስለማታገባ ከልጃገረድ ጓደኞቿ ጋራ ወደ ተራሮች ሄደው አለቀሱ።

39 ከሁለት ወር በኋላ ወደ አባቷ ተመለሰች፤ እርሱም የተሳለውን አደረገ፤ ድንግልም ነበረች። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ይህ በእስራኤል ልማድ ሆኖ፣

40 የእስራኤል ወጣት ሴቶች የገለዓዳዊውን የዮፍታሔን ልጅ በማሰብ በየዓመቱ እየወጡ የአራት ቀን ሐዘን ያደርጉላታል።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告