Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

መሳፍንት 10 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


ቶላ

1 ከአቢሜሌክ በኋላ ከይሳኮር ነገድ የሆነ የዱዲ ልጅ፣ የፎሖ ልጅ ቶላ እስራኤልን ለማዳን ተነሣ፤ እርሱም በኰረብታማው በኤፍሬም አገር ሳምር በምትባል መንደር ይኖር ነበር።

2 ቶላ በእስራኤል ላይ ሃያ ሦስት ዓመት በፈራጅነት ከተቀመጠ በኋላ ሞተ፤ በሳምርም ተቀበረ።


ኢያዕር

3 ከቶላ ቀጥሎ ገለዓዳዊው ኢያዕር ተነሣ፤ እርሱም በእስራኤል ላይ ሃያ ሁለት ዓመት በፈራጅነት ተቀመጠ።

4 ኢያዕር በሠላሳ አህዮች የሚጋልቡ ሠላሳ ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ ልጆቹም እስከ ዛሬ ድረስ የኢያዕር መንደሮች ተብለው የሚጠሩ ሠላሳ ከተሞች በገለዓድ ምድር ነበሯቸው።

5 ኢያዕር ሞተ፤ በቃሞንም ተቀበረ።


ዮፍታሔ

6 እስራኤላውያን እንደ ገና በእግዚአብሔር ላይ ክፉ ድርጊት ፈጸሙ፤ በኣልንና አስታሮትን እንዲሁም የአራምን፣ የሲዶናን፣ የሞዓብን፣ የአሞንንና የፍልስጥኤማውያንን አማልክት አመለኩ፤ እስራኤላውያን እግዚአብሔርን ስለ ተዉና ስላላገለገሉት፣

7 እግዚአብሔርም ተቈጣቸው፤ በፍልስጥኤማውያንና በአሞናውያን እጅ ሸጣቸው፤

8 እነርሱም በዚያ ዓመት ሰበሯቸው፤ አደቀቋቸውም፤ ለዐሥራ ስምንት ዓመታት ከዮርዳኖስ ማዶ ባለው የአሞራውያን ምድር፣ በገለዓድ የነበሩትን እስራኤላውያንን ሁሉ አሠቃዩአቸው።

9 እንዲሁም አሞናውያን ይሁዳን፣ ብንያምንና የኤፍሬምን ቤት ለመውጋት ዮርዳኖስን ስለ ተሻገሩ እስራኤላውያን እጅግ ተጨነቁ።

10 ከዚያም እስራኤላውያን፣ “አንተን አምላካችንን በመተው የበኣልን አማልክት በማምለካችን አንተን በድለናል” ብለው ወደ እግዚአብሔር ጮኹ።

11 እግዚአብሔርም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ግብጻውያን፣ አሞራውያን፣ አሞናውያን፣ ፍልስጥኤማውያን፣

12 ሲዶናውያን፣ አማሌቃውያንና ማዖናውያን አሠቃዩአችሁ፤ እናንተም እንድረዳችሁ ወደ እኔ ጮኻችሁ፤ ታዲያ እኔ ከእጃቸው አላዳንኋችሁምን?

13 እናንተ ግን እኔን ትታችሁ ሌሎች አማልክትን አመለካችሁ፤ ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲያ አላድናችሁም፤

14 ሂዱና ወደ መረጣችኋቸው አማልክት ጩኹ፤ መከራ በሚያገኛችሁ ጊዜ እስኪ ያድኗችሁ።”

15 እስራኤላውያንም እግዚአብሔርን፣ “ኀጢአት ሠርተናል፤ መልካም መስሎ የታየህን አድርግብን፤ እባክህን የዛሬን ብቻ አድነን” አሉት።

16 ከዚያም በመካከላቸው ያሉትን ባዕዳን አማልክት አስወገዱ፤ እግዚአብሔርንም አመለኩ፤ እግዚአብሔርም እስራኤል ስትጐሳቈል ዝም ብሎ ማየት አልቻለም።

17 አሞናውያን ለጦርነት ዝግጁ ሆነው በገለዓድ በሰፈሩ ጊዜ፣ እስራኤላውያንም እንደዚሁ ተሰብስበው በምጽጳ ሰፈሩ።

18 የገለዓድ ሕዝብ አለቆችም እርስ በርሳቸው፣ “በአሞናውያን ላይ ጦርነቱን የሚጀምር ሰው በገለዓድ ነዋሪዎች ሁሉ ላይ አለቃ ይሆናል” ተባባሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告