መሳፍንት 1 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምእስራኤላውያን ከቀሩት ከነዓናውያን ጋራ ያደረጉት ውጊያ 1 ኢያሱ ከሞተ በኋላ እስራኤላውያን፣ “ከነዓናውያንን ለመውጋት ማን ቀድሞ ይውጣልን?” ብለው እግዚአብሔርን ጠየቁ። 2 እግዚአብሔርም፣ “ይሁዳ ቀድሞ ይውጣ፤ እነሆ ምድሪቱን በእጁ አሳልፌ ሰጥቼዋለሁ” በማለት መለሰ። 3 የይሁዳም ሰዎች ወንድሞቻቸውን የስምዖንን ልጆች፣ “ከነዓናውያንን ለመውጋት ድርሻችን ወደ ሆነው ምድር ዐብረን እንውጣ፤ እኛም እንደዚሁ ድርሻችሁ ወደ ሆነው ምድር ዐብረናችሁ እንወጣለን” አሏቸው፤ ስለዚህም የስምዖን ሰዎች ዐብረዋቸው ሄዱ። 4 ይሁዳ በከነዓናውያንና በፌርዛውያን ላይ ወጣ፤ እግዚአብሔርም በእጃቸው አሳልፎ ሰጣቸው፤ ቤዜቅ በተባለውም ስፍራ ዐሥር ሺሕ ሰው ገደሉ። 5 በዚህም አዶኒቤዜቅን አግኝተው ተዋጉት፤ ከነዓናውያንንና ፌርዛውያንን ድል አደረጉ። 6 አዶኒቤዜቅም ከዚያ ሸሸ፤ እነርሱ ግን አሳድደው ያዙት፤ የእጆቹንና የእግሮቹንም አውራ ጣቶች ቈረጡ። 7 ከዚያም አዶኒቤዜቅ፣ “የእጃቸውና የእግራቸው አውራ ጣቶች የተቈረጡባቸው ሰባ ነገሥታት ከገበታዬ ሥር የወደቀ ፍርፋሪ ይለቃቅሙ ነበር፤ አሁን ግን እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ የፈጸምሁትን አመጣብኝ” አለ፤ እነርሱም ወደ ኢየሩሳሌም አመጡት፤ በዚያም ሞተ። 8 የይሁዳ ሰዎች ኢየሩሳሌምን ወግተው ያዟት፤ ከተማዪቱንም በሰይፍ ስለት መተው፣ በእሳት አቃጠሏት። 9 ከዚያም በኋላ የይሁዳ ሰዎች በኰረብታማው አገር፣ በኔጌብና በምዕራቡ ኰረብታ ግርጌ የሚኖሩትን ከነዓናውያንን ለመውጋት ወረዱ፤ 10 ቀደም ሲል ቂርያት አርባቅ ተብላ በምትጠራው በኬብሮን በሚኖሩት ከነዓናውያን ላይ ዘመቱ፤ ሴሲንን፣ አኪመንንና ተላሚንን ድል አደረጉ። 11 ከዚያም ቀደም ሲል ቂርያትሤፍር ተብላ በምትጠራው በዳቤር በሚኖሩት ሰዎች ላይ ዘመቱ። 12 ካሌብም፣ “ቂርያትሤፍርን ወግቶ ለሚይዛት ሰው ልጄን ዓክሳንን እድርለታለሁ” አለ። 13 በዚህ ጊዜ የካሌብ ወንድም የቄኔዝ ልጅ ጎቶንያል ከተማዪቱን ያዘ፤ ካሌብም ልጁን ዓክሳንን ዳረለት። 14 እርሷም ወደ ጎቶንያል በመጣች ጊዜ፣ አባቷ የዕርሻ መሬት እንዲሰጠው ይለምነው ዘንድ አጥብቃ ነገረችው፤ ካሌብም እርሷ ከአህያዋ ላይ እንደ ወረደች “ምን እንዳደርግልሽ ትፈልጊያለሽ?” ሲል ጠየቃት። 15 እርሷም፣ “እባክህ፤ ባርከኝ፤ በኔጌብ መሬት እንደ ሰጠኸኝ ሁሉ፣ አሁንም የውሃ ምንጭ ስጠኝ” አለችው፤ ካሌብም የላይኛውንና የታችኛውን ምንጮች ሰጣት። 16 የቄናዊው የሙሴ ዐማት ዝርያዎች ከዓራድ አጠገብ በኔጌብ ውስጥ በይሁዳ ምድረ በዳ ካሉት ሕዝቦች ጋራ ዐብረው ለመኖር፣ ከይሁዳ ሰዎች ጋራ በመሆን ከባለ ዘንባባዋ ከተማ ከኢያሪኮ ወጡ። 17 የይሁዳ ሰዎች ከወንድሞቻቸው ከስምዖን ልጆች ጋራ ሆነው በጻፋት በሚኖሩት ከነዓናውያን ላይ ዘመቱ፤ ከተማዪቱንም ፈጽሞ ደመሰሷት፤ ስለዚህ ከተማዪቱ ሖርማ ተብላ ተጠራች። 18 ደግሞም የይሁዳ ሰዎች ጋዛ፣ አስቀሎና፣ አቃሮን የተባሉትን ከተሞች ከነግዛቶቻቸው ያዙ። 19 እግዚአብሔር ከይሁዳ ሰዎች ጋራ ነበር፤ ስለዚህ ኰረብታማውን አገር ያዙ፤ ነገር ግን በረባዳው ምድር የሚኖሩት ሰዎች ከብረት የተሠሩ ሠረገሎች ስለ ነበሯቸው ከዚያ አሳድደው ሊያስወጧቸው አልቻሉም። 20 ሙሴ ባዘዘው መሠረት ኬብሮን ለካሌብ ተሰጠች፤ እርሱም ሦስቱን የዔናቅ ልጆች ከውስጧ አሳደደ። 21 የብንያም ልጆች በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን ኢያቡሳውያንን ከዚያ ሊያስወጧቸው አልቻሉም፤ ስለዚህ ኢያቡሳውያን እስከ ዛሬ ድረስ ከብንያማውያን ጋራ በዚያ ዐብረው ይኖራሉ። 22 የዮሴፍ ወገን ደግሞ ቤቴልን ወጉ፤ እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋራ ነበር። 23 የዮሴፍም ወገን ቀደም ሲል ሎዛ ትባል ወደ ነበረችው ወደ ቤቴል ከተማ ሰላዮችን በላኩ ጊዜ፣ 24 ሰላዮቹም አንድ ሰው ከከተማዪቱ ሲወጣ አይተው፤ “የከተማዪቱን መግቢያ አሳየን፤ እኛም ምሕረት እናደርግልሃለን” አሉት። 25 እርሱም አሳያቸው፤ እነርሱም ከሰውየውና ከቤተ ሰቡ በቀር የከተማዪቱን ሕዝብ በሰይፍ ስለት ፈጁ። 26 ሰውየውም ወደ ኬጢያውያን ምድር ሄዶ ከተማ ሠራ፤ ስሟንም ሎዛ ብሎ ጠራት፤ እስከ ዛሬም የምትጠራው በዚሁ ስም ነው። 27 የምናሴ ነገድ ግን በቤትሳን፣ በታዕናክ፣ በዶር፣ በይብለዓም፣ በመጊዶንና በየአካባቢያቸው ያሉት መንደሮች ነዋሪውን ሕዝብ ስላላስወጡ፣ ከነዓናውያን ኑሯቸውን በዚያው ለማድረግ ወሰኑ። 28 እስራኤላውያን በበረቱ ጊዜ ግን ከነዓናውያንን የጕልበት ሥራ እንዲሠሩ አስገደዷቸው እንጂ ፈጽሞ አላስወጧቸውም። 29 እንደዚሁም የኤፍሬም ወገኖች በጌዝር የሚኖሩትን ከነዓናውያንን ማስወጣት አልቻሉም፤ ስለዚህ ከነዓናውያን በመካከላቸው እዚያው መኖርን ቀጠሉ። 30 ዛብሎንም እንደዚሁ በቂድሮንና በነህሎል የነበሩትን በመካከላቸው የቀሩትን ከነዓናውያንን አላስወጣም፤ ነገር ግን የጕልበት ሥራ እንዲሠሩ አስገደዳቸው። 31 አሴርም በዓኮ፣ በሲዶን፣ በአሕላብ፣ በአክዚብ፣ በሒልባ፣ በአፌቅና በረአብ የሚኖሩትን አላስወጣም። 32 በዚህ ምክንያት የአሴር ሕዝብ በምድሪቱ ካሉት ከነዓናውያን ጋራ ዐብረው ኖሩ። 33 ንፍታሌምም በቤትሳሚስና በቤትዓናት የሚኖሩትን አላስወጣም፤ ስለዚህ የንፍታሌም ነገድ በምድሪቱ ከሚኖሩት ከነዓናውያን ጋራ ዐብረው ኖሩ፤ ይሁን እንጂ በቤትሳሚስና በቤትዓናት የሚኖሩት ለእነርሱ የጕልበት ሥራ ተገድደው ይሠሩ ነበር። 34 የዳን ነገድ በኰረብታማው ምድር ብቻ እንዲወሰን እንጂ ወደ ሜዳማው አገር እንዲወርድ አሞራውያን አልፈቀዱለትም። 35 አሞራውያንም በሔሬስ ተራራ፣ በኤሎንና በሻዓልቢም ኑሯቸውን ቀጠሉ፤ ይሁን እንጂ የዮሴፍ ወገን በበረታ ጊዜ ተገድደው የጕልበት ሥራ ከመሥራት አላመለጡም። 36 የአሞራውያን ድንበር አቅራቢያም መተላለፊያ እስከ ሴላዕና ከዚያም የሚያልፍ ነበር። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.