Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ዮሐንስ 19 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


ኢየሱስ እንዲሰቀል ተፈረደበት
19፥1-16 ተጓ ምብ – ማቴ 27፥27-31 ፤ ማር 15፥16-20

1 ጲላጦስም ኢየሱስን ወስዶ አስገረፈው።

2 ወታደሮችም የእሾኽ አክሊል ጐንጕነው በራሱ ላይ አደረጉ፤ ሐምራዊ ልብስም አለበሱት፤

3 እየተመላለሱም፣ “የአይሁድ ንጉሥ ሆይ! ሰላም ለአንተ ይሁን” እያሉ በጥፊ ይመቱት ነበር።

4 ጲላጦስም እንደ ገና ወደ ውጭ ወጥቶ፣ “እንግዲህ ወደ እናንተ ያወጣሁት ለክስ የሚያደርስ ወንጀል እንዳላገኘሁበት እንድታውቁ ነው” አላቸው።

5 ኢየሱስ የእሾኽ አክሊል ደፍቶ ሐምራዊ ልብስም ለብሶ ወጣ፤ ጲላጦስም፣ “እነሆ፤ ሰውየው!” አላቸው።

6 የካህናት አለቆችና አገልጋዮቻቸውም ባዩት ጊዜ፣ “ስቀለው! ስቀለው!” እያሉ ጮኹ። ጲላጦስ ግን፣ “እናንተ ወስዳችሁ ስቀሉት፤ በእኔ በኩል ለክስ የሚያደርስ ወንጀል አላገኘሁበትም” አላቸው።

7 አይሁድም፣ “እኛ ሕግ አለን፤ ራሱን የእግዚአብሔር ልጅ ስላደረገ በሕጋችን መሠረት መሞት አለበት” አሉ።

8 ጲላጦስ ይህን ሲሰማ የባሰውኑ ፈራ፤

9 ወደ ግቢው ተመልሶ ኢየሱስን፣ “ከየት ነው የመጣኸው?” በማለት ጠየቀው፤ ኢየሱስ ግን ምንም አልመለሰለትም።

10 ጲላጦስም፣ “አታናግረኝምን? ልፈታህ ወይም ልሰቅልህ ሥልጣን እንዳለኝ አታውቅም?” አለው።

11 ኢየሱስም፣ “ከላይ ባይሰጥህ ኖሮ በእኔ ላይ ሥልጣን ባልኖረህ ነበር፤ ስለዚህ ለአንተ አሳልፎ የሰጠኝ ሰው የባሰ ኀጢአት አለበት” አለው።

12 ከዚያ በኋላ ጲላጦስ ኢየሱስን ሊፈታው ፈለገ፤ አይሁድ ግን፣ “ይህን ሰው ብትፈታው የቄሳር ወዳጅ አይደለህም፤ ራሱን ንጉሥ የሚያደርግ የቄሳር ተቃዋሚ ነው” በማለት ጩኸታቸውን ቀጠሉ።

13 ጲላጦስም ይህን ሲሰማ ኢየሱስን ወደ ውጭ አወጣው፤ “የድንጋይ ንጣፍ” በተባለ፣ በአራማይክ ቋንቋ “ገበታ” ብለው በሚጠሩት ስፍራ፣ በፍርድ ወንበር ላይ ተቀመጠ።

14 ቀኑ የፋሲካ በዓል መዘጋጃ፣ ጊዜውም ከቀኑ ስድስት ሰዓት ያህል ነበር። ጲላጦስም አይሁድን፣ “እነሆ፤ ንጉሣችሁ” አላቸው።

15 እነርሱ ግን፣ “አስወግደው! አስወግደው! ስቀለው!” እያሉ ጮኹ። ጲላጦስም፣ “ንጉሣችሁን ልስቀለውን?” አለ። የካህናት አለቆችም፣ “ከቄሳር በቀር ሌላ ንጉሥ የለንም” ብለው መለሱለት።

16 በመጨረሻም ጲላጦስ እንዲሰቅሉት አሳልፎ ሰጣቸው። ወታደሮቹም ኢየሱስን ይዘው ወሰዱት፤


ስቅለት
19፥17-24 ተጓ ምብ – ማቴ 27፥33-44 ፤ ማር 15፥22-32 ፤ ሉቃ 23፥33-43

17 እርሱም የራሱን መስቀል ተሸክሞ በአራማይክ “ጎልጎታ” ተብሎ ወደሚጠራው “የራስ ቅል” ወደተባለው ቦታ ወጣ።

18 በዚያም ሰቀሉት፤ ከርሱም ጋራ ሁለት ሰዎች፣ አንዱን በዚህ በኩል፣ ሌላውን በዚያ በኩል፣ ኢየሱስንም በመካከል አድርገው ሰቀሉ።

19 ጲላጦስም ጽሑፍ ጽፎ በመስቀሉ ላይ አንጠለጠለው፤ ጽሑፉም፣ “የናዝሬቱ ኢየሱስ፣ የአይሁድ ንጉሥ” የሚል ነበር።

20 ኢየሱስ የተሰቀለበት ቦታ ከከተማው አጠገብ ስለ ነበር ብዙዎቹ አይሁድ ጽሑፉን አነበቡት፤ ጽሑፉም፣ በአራማይክና በላቲን፣ በግሪክም ነበር።

21 የአይሁድ የካህናት አለቆች ጲላጦስን በመቃወም፣ “እርሱ፣ ‘የአይሁድ ንጉሥ ነኝ’ እንዳለ ጻፍ እንጂ ‘የአይሁድ ንጉሥ’ ብለህ አትጻፍ” አሉት።

22 ጲላጦስም፣ “በቃ፤ የጻፍሁትን ጽፌአለሁ” ብሎ መለሰ።

23 ወታደሮቹ ኢየሱስን ከሰቀሉ በኋላ፣ እጀ ጠባቡ ሲቀር፣ ልብሱን ወስደው ለእያንዳንዱ አንድ አንድ እንዲዳረስ ለአራት ተከፋፈሉት፤ እጀ ጠባቡም ከላይ እስከ ታች አንድ ወጥ ሆኖ ያለ ስፌት የተሠራ ነበር።

24 ስለዚህ፣ “ዕጣ ተጣጥለን ለሚደርሰው ይድረስ እንጂ አንቅደደው” ተባባሉ። ይህም የሆነው፣ “ልብሴን ተከፋፈሉት፤ በእጀ ጠባቤም ላይ ዕጣ ተጣጣሉ” የሚለው የመጽሐፍ ቃል እንዲፈጸም ነው። ወታደሮቹ ያደረጉትም ይህንኑ ነው።

25 በኢየሱስ መስቀል አጠገብ እናቱና የእናቱ እኅት፣ እንዲሁም የቀለዮጳ ሚስት ማርያምና መግደላዊት ማርያም ቆመው ነበር።

26 በዚያም ኢየሱስ እናቱንና የሚወድደውም ደቀ መዝሙር አጠገቧ ቆሞ ሲያያቸው እናቱን፣ “አንቺ ሴት ሆይ፤ ልጅሽ ይኸው” አላት፤

27 ደቀ መዝሙሩንም፣ “እናትህ ይህችው” አለው። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ይህ ደቀ መዝሙር ወደ ቤቱ ወሰዳት።


የኢየሱስ መሞት
19፥29-30 ተጓ ምብ – ማቴ 27፥48-50 ፤ ማር 15፥36-37 ፤ ሉቃ 23፥36

28 ከዚያም ኢየሱስ ሁሉ ነገር እንደ ተፈጸመ ዐውቆ፣ የመጽሐፍ ቃል እንዲፈጸም፣ “ተጠማሁ” አለ።

29 በዚያም የኮመጠጠ ወይን የሞላበት ዕቃ ተቀምጦ ነበር፤ እነርሱም ሰፍነግ በወይን ጠጅ ነክረው፣ በሂሶጵ ዘንግ ወደ አፉ አቀረቡለት፤

30 ኢየሱስም ኮምጣጤውን ከተቀበለ በኋላ፣ “ተፈጸመ” አለ፤ ራሱን አዘንብሎ፣ መንፈሱን አሳልፎ ሰጠ።

31 ዕለቱ ለሰንበት መዘጋጃ ቀን ነበር። አይሁድ፣ የተሰቀሉት ሰዎች ሬሳ በሰንበት ቀን በመስቀል ላይ እንዳይውል ስለ ፈለጉና ያም የተለየ ሰንበት ስለ ነበር፣ የተሰቀሉት ሰዎች ጭናቸው ተሰብሮ በድናቸው እንዲወርድ ጲላጦስን ለመኑት።

32 ስለዚህም ወታደሮቹ መጥተው ከክርስቶስ ጋራ ተሰቅሎ የነበረውን የመጀመሪያውን ሰው ጭን ሰበሩ፤ ደግሞም የሌላውን ጭን ሰበሩ።

33 ወደ ኢየሱስ በመጡ ጊዜ ግን ሞቶ ስላገኙት ጭኖቹን አልሰበሩም፤

34 ነገር ግን ከወታደሮቹ አንዱ የኢየሱስን ጐን በጦር ወጋው፤ ወዲያውም ደምና ውሃ ፈሰሰ።

35 ይህን ያየው ሰው ምስክርነቱን ሰጥቷል፤ ምስክርነቱም እውነት ነው፤ እውነትን እንደሚናገርም ያውቃል፤ እናንተም እንድታምኑ ይመሰክራል።

36 ይህም የሆነው፣ መጽሐፍ፣ “ከዐጥንቱ አንድም አይሰበርም” ያለው እንዲፈጸም፣

37 ሌላውም መጽሐፍ፣ “የወጉትም ያዩታል” ስለሚል ነው።


የኢየሱስ መቀበር
19፥38-42 ተጓ ምብ – ማቴ 27፥57-61 ፤ ማር 15፥42-47 ፤ ሉቃ 23፥50-56

38 ከዚህ በኋላ የአርማትያሱ ዮሴፍ የኢየሱስን በድን ለመውሰድ ጲላጦስን ለመነው፤ ዮሴፍም አይሁድን ስለ ፈራ በስውር የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ነበር። እርሱም ጲላጦስን ካስፈቀደ በኋላ መጥቶ በድኑን ወሰደ።

39 ከዚህ ቀደም በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጥቶ የነበረው ኒቆዲሞስ አንድ መቶ ሊትር ያህል የሚመዝን የከርቤና የአደስ ቅልቅል ይዞ መጣ።

40 እነርሱም የኢየሱስን በድን ወስደው እንደ አይሁድ አገናነዝ ልማድ ከሽቱ ጋራ ከተልባ እግር በተሠራ ጨርቅ ከፈኑት።

41 ኢየሱስ በተሰቀለበት ቦታም የአትክልት ስፍራ ነበር፤ በአትክልቱም ስፍራ ማንም ያልተቀበረበት አዲስ መቃብር ነበር።

42 ዕለቱ ለአይሁድ የሰንበት መዘጋጃ ቀን ስለ ነበርና መቃብሩም ቅርብ ስለ ነበር ኢየሱስን በዚያ ቀበሩት።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告