Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ኢዮብ 8 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


በልዳዶስ

1 ሹሐዊውም በልዳዶስ እንዲህ ሲል መለሰ፤

2 “እንዲህ ያለውን ነገር የምትናገረው፣ ቃልህም እንደ ብርቱ ነፋስ የሚሆነው እስከ መቼ ነው?

3 እግዚአብሔር ፍትሕን ያጣምማልን? ሁሉን ቻይ አምላክስ ጽድቅን ያጣምማልን?

4 ልጆችህ በርሱ ላይ ኀጢአት ሠርተው ከሆነ፣ ለኀጢአታቸው ቅጣት አሳልፎ ሰጥቷቸዋል።

5 ነገር ግን አንተ ወደ እግዚአብሔር ብትመለከት፣ ሁሉን ቻይ አምላክን ብትማፀን፣

6 ንጹሕና ጻድቅ ብትሆን፣ እርሱ ስለ አንተ አሁኑኑ ይነሣል፤ ወደ ተገቢውም ስፍራህ ይመልስሃል።

7 ጅማሬህ አነስተኛ ቢመስልም፣ ፍጻሜህ እጅግ ታላቅ ይሆናል።

8 “የቀደመውን ትውልድ ጠይቅ፤ አባቶቻቸውም የደረሱበትን መርምረህ አግኝ፤

9 እኛ ትናንት ስለ ተወለድን አንዳች አናውቅምና፤ ዘመናችንም በምድር ላይ እንደ ጥላ ነው።

10 እነርሱ የሚያስተምሩህና የሚነግሩህ፣ ከልቦናቸውም ቃልን የሚያወጡ አይደሉምን?

11 ደንገል ረግረግ በሌለበት ስፍራ ይበቅላልን? ቄጠማስ ውሃ በሌለበት ይለመልማልን?

12 ገና በማደግ ላይ እያለ ሳይታጨድ፣ ከሌሎች ሣሮች ፈጥኖ ይደርቃል።

13 እግዚአብሔርን የሚረሱ መጨረሻቸው እንዲህ ነው፤ አምላክ የለሽ ኑሮ የሚኖሩም ሁሉ ተስፋቸው ትጠፋለች።

14 መተማመኛው ቀጭን ክር፣ ድጋፉም የሸረሪት ድር ነው።

15 ድሩ ላይ ቢደገፍ ይበጠስበታል፤ አጥብቆም ቢይዘው አይጸናም።

16 ውሃ እንደ ጠገበ ተክል፣ ፀሓይ እየሞቀው፣ ቅርንጫፉን ሁሉ በአትክልቱ ስፍራ ላይ ይዘረጋል።

17 ሥሩን በድንጋይ ክምር ላይ ይጠመጥማል፤ በዐለትም መካከል ስፍራ ያበጃል።

18 ከስፍራው ሲወገድ ግን፣ ያ ቦታ ‘አይቼህ አላውቅም’ ብሎ ይክደዋል።

19 እነሆ፤ ሕይወቱ በዚህ ያከትማል፤ ሌሎች አትክልትም ከመሬት ይበቅላሉ።

20 “እነሆ፤ እግዚአብሔር እንከን የሌለበትን ሰው አይጥልም፤ የክፉዎችንም እጅ አያበረታም፤

21 እንደ ገና አፍህን በሣቅ፣ ከንፈሮችህንም በእልልታ ይሞላል።

22 ጠላቶችህ ኀፍረት ይለብሳሉ፤ የክፉዎችም ድንኳን ይጠፋል።”

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告