Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ኢዮብ 42 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


ኢዮብ

1 ኢዮብም እንዲህ ሲል ለእግዚአብሔር መለሰ፤

2 “አንተ ሁሉን ማድረግ እንደምትችል፣ ዕቅድህም ከቶ እንደማይሰናከል ዐወቅሁ።

3 አንተ፣ ‘ያለ ዕውቀት ዕቅዴን የሚያደበዝዝ ይህ ማን ነው?’ አልኸኝ፤ በርግጥ ያልገባኝን ነገር፣ የማላውቀውንና ላስተውለው የማልችለውን ጕዳይ ተናገርሁ።

4 “ ‘ስማኝ፣ ልናገር እኔ እጠይቃለሁ፤ አንተ ትመልስልኛለህ’ አልኸኝ።

5 ጆሮዬ ስለ አንተ ሰምታ ነበር፤ አሁን ግን ዐይኔ አየችህ።

6 ስለዚህ ራሴን እንቃለሁ፤ በትቢያና በዐመድ ላይ ተቀምጬ ንስሓ እገባለሁ።”


መደምደሚያ

7 እግዚአብሔር ይህን ለኢዮብ ከተናገረ በኋላ፣ ቴማናዊውን ኤልፋዝን እንዲህ አለው፤ “እንደ አገልጋዬ እንደ ኢዮብ ስለ እኔ ቅን ነገር ስላልተናገራችሁ፣ ቍጣዬ በአንተና በሁለቱ ባልንጀሮችህ ላይ ነድዷል።

8 አሁን እንግዲህ ሰባት ወይፈኖችና ሰባት አውራ በጎች ይዛችሁ ወደ አገልጋዬ ወደ ኢዮብ ሂዱ፤ የሚቃጠል መሥዋዕትም ስለ ራሳችሁ አቅርቡ። እንደ አሳፋሪ ተግባራችሁ እንዳላደርግባችሁ አገልጋዬ ኢዮብ ስለ እናንተ ይጸልያል፤ እኔም ጸሎቱን እቀበላለሁ፤ እንደ አገልጋዬ እንደ ኢዮብ ስለ እኔ ቅን ነገር አልተናገራችሁምና።”

9 ቴማናዊው ኤልፋዝ፣ ሹሐዊው በልዳዶስና ናዕማታዊው ሶፋር እግዚአብሔር እንደ ተናገራቸው አደረጉ፤ እግዚአብሔርም የኢዮብን ጸሎት ተቀበለ።

10 ኢዮብ ለወዳጆቹ ከጸለየ በኋላ፣ እግዚአብሔር እንደ ገና አበለጸገው፤ ቀድሞ በነበረው ፈንታ ዕጥፍ አድርጎ ሰጠው።

11 ወንድሞቹና እኅቶቹ፣ ቀድሞም ያውቁት የነበሩ ሁሉ ወደ እርሱ መጡ፤ በቤቱም ከርሱ ጋራ ምግብ በሉ። እነርሱም ሐዘናቸውን ገለጡለት፤ እግዚአብሔርም ካመጣበት መከራ ሁሉ አጽናኑት፤ እያንዳንዳቸውም ጥሬ ብርና የወርቅ ቀለበት ሰጡት።

12 እግዚአብሔርም ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛውን የኢዮብን ሕይወት ባረከ። እርሱም ዐሥራ አራት ሺሕ በጎች፣ ስድስት ሺሕ ግመሎች፣ አንድ ሺሕ ጥማድ በሬዎች፣ አንድ ሺሕ እንስት አህዮችም ነበሩት።

13 ደግሞም ሰባት ወንዶችና ሦስት ሴቶች ልጆች ነበሩት፤

14 የመጀመሪያዋን ይሚማ፣ ሁለተኛዋን ቃሥያ፣ ሦስተኛዋንም አማልቶያስ ቂራስ ብሎ ሰየማቸው።

15 እንደ ኢዮብ ሴቶች ልጆች የተዋቡ ሴቶች በምድሪቱ ሁሉ አልተገኙም፤ አባታቸውም ከወንድሞቻቸው ጋራ ርስት ሰጣቸው።

16 ከዚህ በኋላ ኢዮብ አንድ መቶ አርባ ዓመት ኖረ፤ ልጆቹንና የልጅ ልጆቹን እስከ አራት ትውልድ ድረስ አየ።

17 ኢዮብም በዚህ ሁኔታ አርጅቶ፣ ዕድሜ ጠግቦ ሞተ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告