Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ኢዮብ 41 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም

1 “ሌዋታንን በመንጠቆ ልታወጣው፣ ወይም ምላሱን በገመድ ልታስረው ትችላለህን?

2 መሰነጊያ በአፍንጫው ልታስገባ፣ ወይም ጕንጩን በሜንጦ ልትበሳ ትችላለህን?

3 እርሱ እንድትምረው ይለማመጥሃል? በለስላሳ ቃላትስ ይናገርሃል?

4 ለዘላለም ባሪያ ታደርገው ዘንድ፣ ከአንተ ጋራ ይዋዋላልን?

5 እንደ ወፍ አልምደኸው ከርሱ ጋራ ልትጫወት ትችላለህ? ወይስ ለሴት አገልጋዮችህ መጫወቻነት ታስረዋለህን?

6 ነጋዴዎችስ በርሱ ላይ ይከራከራሉን? ለቸርቻሪዎችስ ያከፋፍሉታል?

7 ቈዳው ላይ ዐንካሴ ልትሰካ፣ ጭንቅላቱንም በዓሣ መውጊያ ጦር ልትበሳ ትችላለህን?

8 እርሱን እስኪ ንካው፣ ግብግቡን ታስታውሳለህ፤ ከቶም አያላምድህም።

9 እርሱን በቍጥጥር ሥር አውላለሁ ማለት ዘበት ነው፤ በዐይን ማየት እንኳ ብርክ ያስይዛል።

10 ሊቀሰቅሰው የሚደፍር የለም፤ ማን ፊቱ ሊቆም ይችላል?

11 ነክቶት በሰላም የሚሄድ ማን ነው? ከሰማይ በታች ማንም የለም።

12 “ስለ ብርታቱና ስለ አካላቱ ውበት፣ ስለ እጅና እግሩ ከመናገር አልቈጠብም።

13 የደረበውን ልብስ ማን ሊያወልቅ ይችላል? ማንስ ሊለጕመው ወደ መንጋጋው ይቀርባል?

14 አስፈሪ ጥርሶቹ የተገጠገጡበትን፣ የአፉን ደጅ ማን ደፍሮ ይከፍታል?

15 ጀርባው፣ አንድ ላይ የተጣበቁ፣ የጋሻ ረድፎች አሉት፤

16 እጅግ የተቀራረቡ ስለ ሆኑ፣ ነፋስ በመካከላቸው አያልፍም፤

17 እርስ በርስ የተገጣጠሙ ናቸው፤ አንዱ ከአንዱ ጋራ ተጣብቋልና ማንም ሊለያያቸው አይችልም።

18 እንጥሽታው የብርሃን ብልጭታ ያወጣል፤ ዐይኖቹም እንደ ማለዳ ጮራ ናቸው።

19 ከአፉ ፍም ይወጣል፤ የእሳት ትንታግ ይረጫል።

20 በሸንበቆ ማገዶ ላይ ከተጣደ ድስት እንደሚወጣ እንፋሎት፣ ከአፍንጫው ጢስ ይትጐለጐላል።

21 እስትንፋሱ ከሰል ያቀጣጥላል፤ የእሳትም ነበልባል ከአፉ ይወጣል።

22 ብርታት በዐንገቱ ውስጥ አለ፤ አሸባሪነትም በፊቱ እመር እመር ይላል።

23 የሥጋው ንብርብር እርስ በርስ የተጣበቀ፣ በላዩ የጸናና ከቦታው የማይናጋ ነው።

24 ደረቱ እንደ ዐለት የጠጠረ፣ እንደ ወፍጮ ድንጋይም የጠነከረ ነው።

25 እርሱ በተነሣ ጊዜ፣ ኀያላን ይርዳሉ፤ በሚንቀሳቀስበትም ጊዜ ወደ ኋላ ያፈገፍጋሉ።

26 ጦር፣ ፍላጻ ወይም ዐንካሴ፣ ሰይፍም ቢያገኘው አንዳች አይጐዳውም።

27 እርሱ ብረትን እንደ አገዳ፣ ናስንም እንደ ነቀዘ ዕንጨት ይቈጥራል።

28 ቀስት አያባርረውም፤ የወንጭፍ ድንጋይም ለርሱ እንደ ገለባ ነው።

29 ቈመጥ በርሱ ፊት እንደ ገለባ ነው፤ ጦር ሲሰበቅ ይሥቃል።

30 የሆዱ ሥር እንደ ሸካራ ገል ነው፤ እንደ መውቂያ መሣሪያም በጭቃ ላይ ምልክት ጥሎ ያልፋል።

31 እንደሚፈላ ምንቸት ጥልቁን ያናውጠዋል፤ ባሕሩንም እንደ ሽቱ ብልቃጥ ያደርገዋል።

32 ያለፈበትን መንገድ ብሩህ ያደርጋል፤ ቀላዩንም ሽበት ያወጣ ያስመስለዋል።

33 ያለ ፍርሀት የተፈጠረ፣ እንደ እርሱ ያለ በምድር ላይ የለም።

34 ከፍ ያሉትን ሁሉ በንቀት ይመለከታል፤ በትዕቢተኞችም ሁሉ ላይ ንጉሥ ነው።”

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告