ኢዮብ 4 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምኤልፋዝ 1 ቴማናዊው ኤልፋዝም እንዲህ ሲል መለሰ፤ 2 “አንድ ሰው ከአንተ ጋራ ለመናገር ቢሞክር፣ ቅር ይልሃልን? ዳሩ ግን ከመናገር ማን ሊቈጠብ ይችላል? 3 እነሆ፤ አንተ ብዙዎችን ታስተምር እንደ ነበር ዐስብ፤ የደከሙትንም እጆች ታበረታ ነበር፤ 4 ቃልህ የተሰናከሉትን ያነሣ ነበር፤ የሚብረከረከውንም ጕልበት ታጸና ነበር። 5 አሁን ግን መከራ አገኘህ፣ አንተም ተስፋ ቈረጥህ፤ ሸነቈጠህ፤ ደነገጥህም። 6 ንጽሕናህ መታመኛህ፣ ቀና አካሄድህም ተስፋህ አይደለምን? 7 “አሁንም አስተውል፤ ንጹሕ ሆኖ የጠፋ ማን ነው? ቅኖችስ መች ተደምስሰው ያውቃሉ? 8 እኔ እንዳየሁ ክፋትን የሚያርሱ፣ መከራንም የሚዘሩ ያንኑ ያጭዳሉ። 9 በእግዚአብሔር እስትንፋስ ይጠፋሉ፤ በቍጣውም ወላፈን ይደመሰሳሉ። 10 አንበሳ ያገሣል፤ ቍጡውም አንበሳ ይጮኻል፤ የደቦል አንበሳው ጥርስ ግን ተሰብሯል። 11 ብርቱው አንበሳ ዐደን በማጣት ይሞታል፤ የአንበሳዪቱም ግልገሎች ይበተናሉ። 12 “ቃል በምስጢር መጣልኝ፤ ጆሮዬም ሹክሹክታውን ሰማች። 13 በሚያስጨንቅ የሌሊት ሕልም ውስጥ፣ ከባድ እንቅልፍም በሰዎች ላይ በወደቀ ጊዜ፣ 14 ፍርሀትና መንቀጥቀጥ ያዘኝ፤ ዐጥንቶቼም ሁሉ ተናወጡ። 15 መንፈስ ሽው ብሎ በፊቴ ዐለፈ፤ የገላዬም ጠጕር ቆመ። 16 እርሱም ቆመ፣ ምን እንደ ሆነ ግን መለየት አልቻልሁም፤ አንድ ቅርጽ በዐይኔ ፊት ነበረ፤ በእርጭታ ውስጥ እንዲህ የሚል ድምፅ ሰማሁ፤ 17 ‘ሥጋ ለባሽ ከእግዚአብሔር ይልቅ ጻድቅ ሊሆን ይችላልን? ሰውስ ከፈጣሪው ይልቅ ንጹሕ ሊሆን ይችላልን? 18 አምላክ በአገልጋዮቹ ላይ እምነት ካልጣለ፣ መላእክቱንም በስሕተታቸው ከወቀሠ፣ 19 ይልቁንስ በጭቃ ቤት የሚኖሩ፣ መሠረታቸው ከዐፈር የሆነ፣ ከብልም ይልቅ በቀላሉ የሚጨፈለቁ እንዴት ይሆኑ? 20 በንጋትና በምሽት መካከል ይደቅቃሉ፤ ሳይታሰብም ለዘላለም ይጠፋሉ። 21 ያለ ጥበብ ይሞቱ ዘንድ፣ የድንኳናቸው ገመድ አልተነቀለምን?’ |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.