ኢዮብ 38 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምእግዚአብሔር ተናገረ 1 እግዚአብሔርም በዐውሎ ነፋስ ውስጥ ሆኖ ለኢዮብ መለሰለት፤ እንዲህም አለው፤ 2 “ዕውቀት በጐደለው ቃል፣ ዕቅዴን የሚያጨልም ይህ ማን ነው? 3 እስኪ እንደ ወንድ ወገብህን ታጠቅ፤ እኔ ልጠይቅህ፣ አንተም መልስልኝ። 4 “ምድርን በመሠረትሁ ጊዜ አንተ የት ነበርህ? በርግጥ የምታስተውል ከሆንህ ንገረኝ። 5 ካወቅህ፣ መጠኗን ለይቶ ማን ወሰነ? በላይዋስ መለኪያ ገመድ የዘረጋ ማን ነው? 6 መሠረቶቿ ምን ላይ ተተከሉ? የማእዘን ድንጋይዋንስ ማን አቆመ? 7 ይህም የሆነው የንጋት ከዋክብት በዘመሩበት ጊዜ፣ መላእክትም እልል ባሉበት ጊዜ ነበር። 8 “ባሕር ከማሕፀን በወጣ ጊዜ፣ በር የዘጋበት ማን ነው? 9 ደመናውን ልብሱ፣ ጨለማንም መጠቅለያው አደረግሁለት፣ 10 ድንበር ወሰንሁለት፤ መዝጊያና መወርወሪያውን አበጀሁለት። 11 ‘እስከዚህ ድረስ ትመጣለህ፤ ማለፍ ግን አትችልም፤ የዕቡይ ማዕበልህም ገደብ ይህ ነው’ አልሁት። 12 “ከተወለድህ ጀምሮ ንጋትን አዝዘህ ታውቃለህን? ወይስ ወጋገን ስፍራውን እንዲይዝ አድርገሃል? 13 በዚህም የምድርን ዳርቻ ይዞ፣ ክፉዎችን ከላይዋ እንዲያራግፍ አድርገሃልን? 14 ምድር ከማኅተም በታች እንዳለ የሸክላ ጭቃ ቅርጿ ይወጣል፤ ቅርጿ እንደ ልብስ ቅርጽ ጐልቶ ይታያል። 15 ክፉዎች ብርሃናቸውን ተከልክለዋል፤ ከፍ ያለው ክንዳቸውም ተሰብሯል። 16 “ወደ ባሕር ምንጭ ወርደህ ታውቃለህን? ወይስ ወደ ጥልቀቱ ገብተህ በመሠረቱ ላይ ተመላልሰሃልን? 17 የሞት ደጆች ተገልጠውልሃልን? የሞትንስ ጥላ በሮች አይተሃልን? 18 የምድርን ስፋት ታውቃለህን? ይህን ሁሉ ዐውቀህ ከሆነ፣ ንገረኝ። 19 “ወደ ብርሃን መኖሪያ የሚያደርሰው መንገድ የትኛው ነው? የጨለማ መኖሪያስ ወዴት ነው? 20 ወደ ማደሪያቸው ልትወስዳቸው ትችላለህን? የመኖሪያቸውን መንገድ ታውቃለህ? 21 ያን ጊዜ ተወልደሃል! ዕድሜህ ትልቅ ነውና፣ አንተስ በርግጥ ሳታውቅ አትቀርም! 22 “ወደ በረዶው መጋዘን ገብተሃልን? የዐመዳዩንስ ማከማቻ አይተሃልን? 23 ይኸውም ለመከራ ጊዜ፣ ለጦርነትና ለውጊያ ቀን ያስቀመጥሁት ነው። 24 መብረቅ ወደሚሠራጭበት ቦታ የሚያደርሰው መንገድ፣ የምሥራቅም ነፋስ በምድር ላይ ወደሚበተንበት ስፍራ የሚወስደው የትኛው ነው? 25 ለዝናብ መውረጃን፣ ለመብረቅም መንገድን ያበጀ ማን ነው? 26 በዚህም ማንም የማይኖርበትን ምድር፣ ሰውም የሌለበትን ምድረ በዳ የሚያጠጣ፣ 27 ባድማውንና በረሓውን መሬት የሚያጠግብ፣ ሣርም እንዲበቅልበት የሚያደርግ ማን ነው? 28 ዝናብ አባት አለውን? የጤዛን ጠብታ ማን ወለደው? 29 በረዶ ከማን ማሕፀን ይወጣል? የሰማዩንስ ዐመዳይ ማን ይወልዳል? 30 ውሆች እንደ ድንጋይ ይጠነክራሉ፤ የጥልቁ ገጽ እንደ በረዶ ይጋገራል። 31 “ፕልያዲስ የተባሉትን ውብ ከዋክብት ልትለጕም፣ ወይም የኦርዮንን ማሰሪያ ልትፈታ ትችላለህን? 32 ማዛሮት የተባለውን የከዋክብት ክምችት በወቅቱ ልታወጣ፣ ወይም ድብ የተባለውን ኮከብና ልጆቹን ልትመራ ትችላለህ? 33 የሰማያትን ሥርዐት ታውቃለህ? ይህንስ በምድር ላይ እንዲሠለጥን ማድረግ ትችላለህ? 34 “ድምፅህን ወደ ደመናት አንሥተህ፣ ራስህን በጐርፍ ማጥለቅለቅ ትችላለህን? 35 መብረቆችን መስደድ ትችላለህ? እነርሱስ፣ ‘እነሆ፤ እዚህ አለን’ ይሉሃል? 36 ለልብ ጥበብን፣ ለአእምሮም ማስተዋልን የሰጠ ማን ነው? 37 ትቢያ ሲጠጥር፣ ጓሎችም እርስ በርስ ሲጣበቁ፣ 38 ደመናትን ለመቍጠር ጥበብ ያለው ማን ነው? የሰማያትንስ የውሃ ገንቦ ዘንበል ማድረግ ማን ይችላል? 39 “ለአንበሳዪቱ ዐድነህ ግዳይ ታመጣለህን? የተራቡ የአንበሳ ግልገሎችንስ ታጠግባለህን? 40 እነርሱ በዋሻ ውስጥ ያደባሉ፤ በደን ውስጥም ይጋደማሉ። 41 ልጆቿ ወደ እግዚአብሔር ሲጮኹ፣ ምግብ ዐጥተው ሲንከራተቱ፣ ለቍራ መብልን የሚሰጥ ማን ነው? |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.