ኢዮብ 37 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም1 “ልቤ በዚህ በኀይል ይመታል፤ ከስፍራውም ዘለል ዘለል ይላል። 2 ስሙ! የድምፁን ጩኸት፣ ከአፉም የሚወጣውን ጕርምርምታ፤ 3 ከሰማይ ሁሉ በታች ብርሃኑን ይለቅቃል፤ እስከ ምድርም ዳርቻ ይልካል። 4 ከዚያም በኋላ የድምፁ ጩኸት ይመጣል፤ በድምፁም ግርማ ያንጐደጕዳል፤ ድምፁ በተሰማ ጊዜ፣ መብረቁን የሚከለክል የለም። 5 የእግዚአብሔር ድምፅ በሚያስደንቅ ሁኔታ ያንጐደጕዳል፤ እኛ የማናስተውለውንም ታላቅ ነገር ያደርጋል። 6 በረዶውን፣ ‘በምድር ላይ ውደቅ’ ውሽንፍሩንም ‘ዶፍህን አውርደው’ ይላል። 7 እርሱ የፈጠራቸው ሰዎች ሁሉ ሥራውን ያውቁ ዘንድ፣ እያንዳንዱ ሰው እንዳይሠራ ይገታዋል። 8 እንስሳት ይጠለላሉ፤ በየዋሻቸውም ይቈያሉ። 9 ዐውሎ ነፋስ ከማደሪያው፣ ብርድም ከብርቱ ነፋስ ይወጣል። 10 የእግዚአብሔር እስትንፋስ በረዶ ያስገኛል፤ ሰፋፊ ውሆች ግግር በረዶ ይሆናሉ። 11 ደመናትን ርጥበት ያሸክማቸዋል፤ መብረቁንም በውስጣቸው ይበትናል። 12 ያዘዘውን ለመፈጸም፣ እርሱ በሚሰጠው መመሪያ፣ በመላው የምድር ገጽ ላይ ይሽከረከራሉ። 13 ሰዎችን ለመቅጣት ደመና ያመጣል፤ ወይም በዚሁ ምድሩን አጠጥቶ ፍቅሩን ይገልጻል። 14 “ኢዮብ ሆይ፤ ይህን ስማ፤ ቆም ብለህ የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ ዐስብ። 15 እግዚአብሔር ደመናትን እንዴት እንደሚቈጣጠር፣ መብረቁንም እንዴት እንደሚያባርቅ ታውቃለህን? 16 ደመናት ሚዛን ጠብቀው እንዴት እንደሚንሳፈፉ፣ በዕውቀቱ ፍጹም የሆነውን፣ የርሱን ድንቅ ሥራ ታውቃለህን? 17 ምድር በደቡብ ነፋስ ጸጥ ባለች ጊዜ፣ ከሙቀት የተነሣ በልብስህ ውስጥ የምትዝለፈለፍ ሆይ፤ 18 ከቀለጠ ናስ እንደ ተሠራ መስተዋት የጠነከረውን ሰማይ ሲዘረጋ፣ ዐብረኸው መዘርጋት ትችል ነበርን? 19 “ከጨለማችን የተነሣ እኛ ጕዳያችንን መግለጽ አንችልም፤ ለርሱ የምንለውን ንገረን። 20 እኔ መናገር እንደ ፈለግሁ ሊነገረው ይገባልን? ይዋጥ ዘንድ የሚጠይቅ ሰው አለን? 21 እንግዲህ ነፋስ ሰማያትን ካጠራ በኋላ፣ እጅግ የምታበራዋን ፀሓይ፣ ሊመለከት የሚችል የለም። 22 እንደ ወርቅ በሚያበራ ክብር ከሰሜን ይወጣል፤ እግዚአብሔር በሚያስፈራ ግርማ ይመጣል። 23 ሁሉን ቻይ አምላክ ከአእምሯችን በላይ ነው፤ በኀይልና በፍርድ ታላቅ ነው፣ ጽድቁም ብዙ ነው፤ ማንንም አይጨቍንም። 24 ስለዚህ፣ ሰዎች ይፈሩታል፤ በልባቸው አስተዋዮች እንደ ሆኑ የሚያስቡትን አይመለከትም?” |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.