Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ኢዮብ 34 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም

1 ኤሊሁ በመቀጠል እንዲህ አለ፤

2 “እናንተ ጠቢባን፣ ቃሌን ስሙ፤ ዐዋቂዎችም አድምጡኝ።

3 ምላስ ምግብን አጣጥሞ እንደሚለይ፣ ጆሮም የንግግርን ለዛ ለይቶ ያውቃል።

4 የሚበጀንን እንምረጥ፣ መልካሙንም ዐብረን እንወቅ።

5 “ኢዮብ እንዲህ ይላል፤ ‘እኔ ንጹሕ ነኝ፤ እግዚአብሔር ግን ፍትሕ ነሣኝ፤

6 እውነተኛ ብሆንም፣ እንደ ውሸታም ተቈጥሬአለሁ፤ በደል ባይኖርብኝም፣ በማይፈወስ ቍስል ተመትቻለሁ።’

7 ፌዝን እንደ ውሃ የሚጠጣት፣ እንደ ኢዮብ ያለ ሰው ማን ነው?

8 ከክፉ አድራጊዎች ጋራ ይተባበራል፤ ከኀጢአተኞችም ጋራ ግንባር ይፈጥራል።

9 ‘እግዚአብሔርን ለማስደሰት መሞከር፣ ለሰው አንዳች አይጠቅምም’ ብሏልና።

10 “ስለዚህ፣ እናንተ አስተዋዮች ስሙኝ፤ ክፋትን ማድረግ ከእግዚአብሔር ዘንድ፣ በደልንም መፈጸም ሁሉን ቻይ አምላክ ይራቅ።

11 ለሰው እንደ ሥራው ይመልስለታል፤ እንደ አካሄዱም ይከፍለዋል።

12 በእውነት እግዚአብሔር ክፋትን አይሠራም፤ ሁሉን ቻይ አምላክ ፍትሕን አያጣምምም።

13 ምድርን እንዲገዛ የሾመው አለን? የዓለምስ ሁሉ ባለቤት ያደረገው ማን ነው?

14 እርሱ መንፈሱን መልሶ ቢወስድ፣ እስትንፋሱንም ወደ ራሱ ቢሰበስብ፣

15 ሥጋ ለባሽ ሁሉ በአንድነት በጠፋ፣ ሰውም ወደ ዐፈር በተመለሰ ነበር።

16 “ማስተዋል ካለህ ይህን ስማ፤ እኔ የምለውንም አድምጥ።

17 ፍትሕን የሚጠላ ሊያስተዳድር ይችላልን? አንተስ ጻድቁንና ኀያል የሆነውን ትኰንናለህ?

18 ነገሥታትን ‘ምናምንቴ ናችሁ፣’ መኳንንትንም፣ ‘ክፉዎች ናችሁ’ የሚላቸው እርሱ አይደለምን?

19 ሁሉም የእጁ ሥራ ስለ ሆኑ፣ እርሱ ለገዦች አያደላም፤ ባለጠጋውንም ከድኻው አብልጦ አይመለከትም።

20 እነርሱም እኩለ ሌሊት ላይ በድንገት ይሞታሉ፤ ሕዝብ ተንቀጥቅጦ ሕይወቱ ያልፋል፤ ኀያላኑም የሰው እጅ ሳይነካቸው ይወገዳሉ።

21 “ዐይኖቹ የሰውን አካሄድ ይመለከታሉ፤ ርምጃውንም ሁሉ ይከታተላሉ።

22 ክፉ አድራጊዎች የሚደበቁበት፣ ጨለማ ስፍራ ወይም የሞት ጥላ የለም።

23 ሰው ለፍርድ ፊቱ ይቀርብ ዘንድ፣ እግዚአብሔር ቀጠሮ አይዝለትም።

24 ያለ ምንም ጥያቄ ኀያላንን ያንኰታኵታል፤ ሌሎችንም በቦታቸው ይሾማል።

25 እርሱ ሥራቸውን ሁሉ ስለሚያውቅ፣ በሌሊት ይገለብጣቸዋል፤ እነርሱም ይደቅቃሉ።

26 ስለ ክፋታቸውም፣ በሰው ሁሉ ፊት ይቀጣቸዋል፤

27 እርሱን ከመከተል ተመልሰዋልና፤ መንገዱንም ችላ ብለዋል።

28 የድኾች ልቅሶ ወደ እርሱ እንዲደርስ ሰበብ ሆኑ፤ የመከረኞችን ጩኸት ሰማ።

29 እርሱ ዝም ቢል፣ ማን ሊፈርድ ይችላል? ፊቱንስ ቢሰውር፣ ማን ሊያየው ይችላል? እርሱ ከሰውም፣ ከሕዝብም በላይ ነው፤

30 ይህም የሆነው ዐመፀኛው ሰው ሕዝቡን እንዳይገዛ፣ ወጥመድም በፊታቸው እንዳይዘረጋ ነው።

31 “ማን ለእግዚአብሔር እንዲህ አለ፤ ‘እኔ በደለኛ ነኝ፤ ከእንግዲህ ግን አልበድልም፤

32 ማየት ያልቻልሁትን አስተምረኝ፤ ኀጢአት ሠርቼ እንደ ሆነም፣ ደግሜ አልሠራም።’

33 ታዲያ አንተ ለመናዘዝ ፈቃደኛ ሳትሆን፤ እግዚአብሔር እንደ ወደድህ ይከፍልሃልን? መወሰን ያለብህ አንተ ነህ እንጂ፣ እኔ አይደለሁም፤ እንግዲህ የምታውቀውን ንገረኝ።

34 “አስተዋዮች ይናገራሉ፤ የሚሰሙኝም ጠቢባን እንዲህ ይሉኛል፤

35 ‘ኢዮብ ያለ ዕውቀት ይናገራል፤ ቃሉም ማስተዋል ይጐድለዋል።’

36 ምነው ኢዮብ እስከ መጨረሻ በተፈተነ ኖሮ! እንደ ክፉ ሰው መልሷልና፤

37 በኀጢአቱም ላይ ዐመፅን ጨምሯል፤ በመካከላችን ሆኖ በንቀት አጨብጭቧል፤ በእግዚአብሔርም ላይ ብዙ ተናግሯል።”

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告