ኢዮብ 33 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም1 “አሁን ግን ኢዮብ ሆይ፣ ንግግሬን ስማ፤ የምለውንም ሁሉ አድምጥ። 2 እንግዲህ አፌን እከፍታለሁ፤ አንደበቴም ይናገራል። 3 ቃሌ ከቅን ልብ ይወጣል፤ ከንፈሬም የማውቀውን በትክክል ይናገራል። 4 የእግዚአብሔር መንፈስ ፈጥሮኛል፤ የሁሉን ቻዩ አምላክ እስትንፋስ ሕይወት ሰጥቶኛል። 5 የምትችል ከሆነ መልስልኝ፤ ተዘጋጅተህም በፊቴ ቁም። 6 በእግዚአብሔር ፊት እኔም እንደ አንተው ነኝ፤ የተፈጠርሁትም ደግሞ ከዐፈር ነው። 7 እኔን መፍራት የለብህም፤ እጄም ሊከብድብህ አይገባም። 8 “በርግጥ የተናገርኸውን አድምጫለሁ፤ እንዲህም ስትል ሰምቻለሁ፤ 9 ‘ኀጢአት የሌለብኝ ንጹሕ ነኝ፤ ከበደል ነጻ ነኝ፤ እድፈትም የለብኝም፤ 10 እግዚአብሔር ግን ሰበብ ፈልጎብኛል፤ እንደ ጠላቱም ቈጥሮኛል፤ 11 እግሬን በግንድ አጣብቋል፤ እንቅስቃሴዬንም ሁሉ ይከታተላል።’ 12 “ነገር ግን እግዚአብሔር ከሰው ስለሚበልጥ፣ ትክክል እንዳልሆንህ እነግርሃለሁ። 13 የሰውን አቤቱታ እንደማይሰማ፣ ለምን ታማርርበታለህ? 14 ሰው ባያስተውለውም፣ እግዚአብሔር በተለያየ መንገድ ይናገራል፤ 15 ሰዎች ዐልጋቸው ላይ ተኝተው ሳሉ፣ ከባድ እንቅልፍ ሲወድቅባቸው፣ በሕልም፣ በሌሊትም ራእይ ይናገራል። 16 በጆሯቸው ይናገራል፤ በማስጠንቀቂያም ያስደነግጣቸዋል፤ 17 ሰውን ከክፉ ሥራው ይመልሳል፤ ከትዕቢት ይጠብቃል፤ 18 ነፍሱን ከጕድጓድ፤ ሕይወቱንም ከሰይፍ ጥፋት ያድናል። 19 “ደግሞም ሰው ታምሞ በዐልጋው ላይ ሳለ፣ በዐጥንቱ የዘወትር ሥቃይ ይገሥጸዋል፤ 20 ያኔም ሕይወቱ መብልን ትጠላለች፤ ነፍሱም ምርጥ ምግብን ትጠየፋለች። 21 እንዳልነበረ ሆኖ ሥጋው ይመነምናል፤ ተሸፍኖ የነበረው ዐጥንቱም ገጥጦ ይወጣል። 22 ነፍሱ ወደ ጕድጓድ፣ ሕይወቱም ወደ ሞት መልእክተኞች ትቀርባለች። 23 ሆኖም ትክክለኛውን መንገድ ለሰው ያመለክት ዘንድ፣ መካከለኛም ይሆንለት ዘንድ፣ ከሺሕ አንድ መልአክ ቢገኝ፣ 24 ለሰውየውም በመራራት፣ ‘ቤዛ አግኝቼለታለሁና፣ ወደ ጕድጓድ እንዳይወርድ አድነው’ ቢለው፣ 25 በዚህ ጊዜ ሥጋው እንደ ሕፃን ልጅ ገላ ይታደሳል፤ ወደ ወጣትነቱም ዘመን ይመለሳል። 26 ወደ እግዚአብሔር ይጸልያል፤ ሞገስም ያገኛል፤ የእግዚአብሔርን ፊት ያያል፤ ሐሤትም ያደርጋል፤ እግዚአብሔር ወደ ጽድቅ ቦታው ይመልሰዋል። 27 ከዚያም ወደ ሰዎች መጥቶ እንዲህ ይላል፤ ‘ኀጢአትን ሠርቻለሁ፤ ትክክል የሆነውን አጣምሜአለሁ፤ ነገር ግን የእጄን አላገኘሁም። 28 ነፍሴ ወደ ጕድጓድ እንዳትወርድ፣ ታድጓታል፤ በሕይወትም ሆኜ ብርሃን አያለሁ።’ 29 “እግዚአብሔር ይህን ሁሉ፣ ሁለት ሦስት ጊዜ ለሰው ያደርጋል። 30 ይኸውም የሕይወት ብርሃን ይበራለት ዘንድ፣ ነፍሱን ከጕድጓድ ለመመለስ ነው። 31 “ኢዮብ ሆይ፤ ልብ ብለህ ስማኝ፤ እኔ ልናገር፤ አንተ ዝም በል። 32 የምትለው ካለህ፣ መልስ ስጠኝ፤ ትክክለኛነትህንም ማወቅ እፈልጋለሁና ተናገር፤ 33 አለዚያ፣ ዝም ብለህ ስማኝ፤ እኔም ጥበብን አስተምርሃለሁ።” |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.