ኢዮብ 31 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም1 “ወደ ኰረዳዪቱ ላለመመልከት፣ ከዐይኔ ጋራ ቃል ኪዳን ገብቻለሁ። 2 ከላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሰው ዕድል ፈንታው፣ ከአርያም ከሁሉን ቻይ አምላክስ ዘንድ ቅርሱ ምንድን ነው? 3 ለኀጢአተኞች ጥፋት፣ ክፉ ለሚያደርጉም መቅሠፍት አይደለምን? 4 እርሱ መንገዴን አያይምን? ርምጃዬንስ ሁሉ አይቈጥርምን? 5 “በሐሰት ሄጄ እንደ ሆነ፣ እግሬም ወደ ሽንገላ ቸኵሎ ከሆነ፣ 6 እግዚአብሔር በጽድቅ ሚዛን ይመዝነኝ፤ ነውር እንደሌለብኝም ይወቅ። 7 አረማመዴ ከመንገድ ወጣ ብሎ፣ ልቤ ዐይኔን ተከትሎ፣ ወይም እጄ ረክሶ ከሆነ፣ 8 የዘራሁትን ሌላ ይብላው፤ ሰብሌም ተነቅሎ ይጥፋ። 9 “ልቤ ሌላዋን ሴት ከጅሎ፣ በባልንጀራዬ ደጅ አድብቼ ከሆነ፣ 10 ሚስቴ የሌላ ሰው እህል ትፍጭ፤ ሌሎች ሰዎችም ይተኟት፤ 11 ይህ አሳፋሪ፣ ፍርድም የሚገባው ኀጢአት ነውና። 12 ይህ የሚያቃጥልና የሚያጠፋ እሳት ነው፤ ቡቃያዬንም ባወደመ ነበር። 13 “ወንዶችና ሴቶች አገልጋዮቼ አቤቱታ ባቀረቡ ጊዜ፣ ፍርድ አዛብቼ ከሆነ፣ 14 እግዚአብሔር ሲነሣ ምን አደርጋለሁ? ሲጠይቀኝስ ምን መልስ እሰጣለሁ? 15 እኔን በማሕፀን ውስጥ የፈጠረኝ እነርሱን የፈጠረ አይደለምን? በሆድ ውስጥ የሠራንስ እርሱ ራሱ አይደለምን? 16 “ለድኻ የሚያስፈልገውን ከልክዬ ከሆነ፣ ወይም የመበለቲቱን ዐይን አፍዝዤ ከሆነ፣ 17 እንጀራዬን ከድኻ አደጉ ጋራ ሳልካፈል፣ ለብቻዬ በልቼ ከሆነ፣ 18 ይልቁን ድኻ አደጉን ከታናሽነቴ ጀምሮ እንደ አባት አሳደግሁት፤ መበለቲቱንም ከተወለድሁ ጀምሮ መንገድ መራኋት፤ 19 በልብስ ዕጦት ሰው ሲጠፋ፣ ወይም ዕርቃኑን ያልሸፈነ ድኻ አይቼ፣ 20 በበጎቼ ጠጕር ስላሞቅሁት፣ ልቡ ባርኮኝ ካልሆነ፣ 21 በአደባባይ ተሰሚነት አለኝ ብዬ፣ በድኻ አደጉ ላይ እጄን አንሥቼ ከሆነ፣ 22 ትከሻዬ ከመጋጠሚያው ይነቀል፤ ክንዴም ከመታጠፊያው ይሰበር፤ 23 የእግዚአብሔርን ቍጣ በመፍራቴ፣ እንዲህ ያሉ ነገሮች መፈጸም አልቻልሁም። 24 “ወርቅን ተስፋ አድርጌ፣ ወይም ንጹሑን ወርቅ፣ ‘አንተ መታመኛዬ ነህ’ ብዬ ከሆነ፣ 25 እጄ ባገኘችው ሀብት፣ በባለጠግነቴም ብዛት ደስ ብሎኝ ከሆነ፣ 26 የፀሓይን ድምቀት አይቼ፣ ወይም የጨረቃን አካሄድ ግርማ ተመልክቼ፣ 27 ልቤ በስውር ተታልሎ፣ ስለ ክብራቸው አፌ እጄን ስሞ ከሆነ፣ 28 ለልዑል እግዚአብሔር ታማኝ አለመሆኔ ነውና፣ ይህም ደግሞ የሚያስቀጣኝ በደል በሆነ ነበር። 29 “በጠላቴ ውድቀት ደስ ብሎኝ፣ በደረሰበትም መከራ ሐሤት አድርጌ እንደ ሆነ፣ 30 እኔ ግን በነፍሱ ላይ ክፉ እንዲመጣ በመራገም፣ አንደበቴን ለኀጢአት ከቶ አሳልፌ አልሰጠሁም። 31 የቤቴ ሰዎች፣ ‘ከኢዮብ ከብት ሥጋ አስቈርጦ፣ ያልጠገበ ማን ነው?’ ብለው ካልሆነ፣ 32 ነገር ግን ቤቴ ለመንገደኛው ዘወትር ክፍት ስለ ነበር፣ መጻተኛው በጐዳና ላይ አያድርም ነበር። 33 ሰዎች እንደሚያደርጉት በደሌን በልቤ በመሰወር፣ ኀጢአቴን ሸሽጌ ከሆነ፣ 34 ሕዝቡን በመፍራት፣ የወገኖቼንም ንቀት በመሸሽ፣ ወደ ደጅ ሳልወጣ፣ ዝም ብዬ ቤት ውስጥ አልተቀመጥሁም። 35 “ምነው የሚሰማኝ ባገኝ! የመከላከያ ፊርማዬ እነሆ፤ ሁሉን ቻይ አምላክ ይመልስልኝ፤ ከሳሼም ክሱን በጽሑፍ ያቅርብ። 36 በርግጥ ትከሻዬ ላይ በደረብሁት፣ እንደ አክሊልም ራሴ ላይ በደፋሁት ነበር። 37 እያንዳንዱን ርምጃዬን በገለጽሁለት፣ እንደ ልዑል እየተንጐራደድሁ በቀረብሁት ነበር። 38 “ዕርሻዬ በእኔ ላይ ጮኻ ከሆነ፣ ትልሞቿ ሁሉ በእንባ ርሰው እንደ ሆነ፣ 39 ፍሬዋን ያለ ዋጋ በልቼ፣ የባለመሬቶቿን ነፍስ አሳዝኜ ከሆነ፣ 40 በስንዴ ፈንታ እሾኽ፣ በገብስም ምትክ ዐረም ይብቀልብኝ።” የኢዮብ ቃል ተፈጸመ። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.