ኢዮብ 30 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም1 “አሁን ግን በዕድሜ ከእኔ የሚያንሱ፣ ከመንጋዬ ጠባቂ ውሾች ጋራ እንዳይቀመጡ፣ አባቶቻቸውን የናቅኋቸው፣ እነዚህ ይሣለቁብኛል። 2 ጕልበት የከዳቸው፣ የክንዳቸው ብርታት ምን ፋይዳ ይሞላልኝ ነበር? 3 ከችጋርና ከራብ የተነሣ ጠወለጉ፤ ሰው በማይኖርበት በረሓ፣ በደረቅም ምድር በሌሊት ተንከራተቱ። 4 ከቍጥቋጦ ምድር ጨው ጨው የሚል አትክልት ለቀሙ፤ ምግባቸውም የክትክታ ሥር ነበር። 5 ከኅብረተ ሰቡ ተለይተው ተባረሩ፤ ሰዎች እንደ ሌባ ይጮኹባቸዋል። 6 በዐለት መካከል በምድር ጕድጓድ፣ በደረቅ ሸለቆ ዋሻ ውስጥ ለመኖር ተገደዱ። 7 በጫካ ውስጥ ያናፋሉ፤ በእሾኻማ ቍጥቋጦ መካከልም ይታፈጋሉ። 8 ስማቸው የማይታወቅ ሞኞች ናቸው፤ ከምድሪቱም ተባርረዋል። 9 “አሁን ግን ልጆቻቸው በዘፈን ይሣለቁብኛል፤ በእነርሱም ዘንድ መተረቻ ሆኛለሁ። 10 ይጸየፉኛል፣ ወደ እኔም አይቀርቡም፤ ያለ ምንም ይሉኝታ በፊቴ ይተፋሉ። 11 አምላክ የቀስቴን አውታር ስላላላውና በመከራም ስለ መታኝ፣ በፊቴ መቈጠብን ትተዋል። 12 በቀኜ በኩል ባለጌዎች ሆ! ብለው ተነሡብኝ፤ ለእግሬም ወጥመድ ዘረጉ፤ የዐፈር ድልድልም አዘጋጁብኝ። 13 መንገድ ዘጉብኝ፤ የሚገታቸው ሳይኖር፣ ሊያጠፉኝ ተነሡ። 14 በሰፊ ንቃቃት ውስጥ እንደሚመጣ ሰው መጡብኝ፤ በፍርስራሽም መካከል እየተንከባለሉ ደረሱብኝ። 15 በድንጋጤ ተውጫለሁ፤ ክብሬ በነፋስ እንደሚወሰድ ተወስዷል፤ በሰላም መኖሬም እንደ ደመና እልም ብሎ ጠፍቷል። 16 “አሁን ነፍሴ በውስጤ ዐለቀች፤ የመከራ ዘመንም ይዞኛል። 17 ደዌ በሌሊት ዐጥንቴን ይበሳል፤ የሚቈረጥመኝም ፋታ አይሰጠኝም። 18 አምላክ በታላቅ ኀይሉ ልብሴን ጨምድዷል፤ በልብሴም ክሳድ ዐንቆ ይዞኛል። 19 እርሱ ጭቃ ውስጥ ጥሎኛል፤ እኔም ከዐፈርና ከዐመድ አልተሻልሁም። 20 “አምላክ ሆይ፤ ወደ አንተ ጮኽሁ፤ ነገር ግን አልመለስህልኝም፤ በፊትህም ቆምሁ፤ አንተ ግን ዝም አልኸኝ። 21 ተመልሰህ ጨካኝ ሆንህብኝ፤ በክንድህም ብርታት አስጨነቅኸኝ። 22 ወደ ላይ ነጥቀህ በነፋስ ፊት አበረርኸኝ፤ በዐውሎ ነፋስም ወዲያ ወዲህ ወዘወዝኸኝ። 23 ለሕያዋን ሁሉ ወደ ተመደበው ስፍራ፣ ወደ ሞት እንደምታወርደኝ ዐውቃለሁ። 24 “የተጐዳ ሰው ተጨንቆ ድረሱልኝ ብሎ ሲጮኽ፣ በርግጥ ክንዱን የሚያነሣበት ማንም የለም። 25 በመከራ ውስጥ ላሉት አላለቀስሁምን? ለድኾችስ ነፍሴ አላዘነችምን? 26 ነገር ግን መልካም ስጠብቅ፣ ክፉ ነገር ደረሰብኝ፤ ብርሃንንም ስጠባበቅ፣ ጨለማ መጣብኝ። 27 በውስጤ ያለው ነውጥ አላቋረጠም፤ የመከራ ዘመንም መጣብኝ። 28 በፀሓይ አይደለም እንጂ፣ ጠቋቍሬ እዞራለሁ፤ በጉባኤ መካከል ቆሜ ለርዳታ እጮኻለሁ። 29 የቀበሮች ወንድም፣ የጕጕቶችም ባልንጀራ ሆኛለሁ። 30 ቈዳዬ ጠቍሮ ተቀረፈ፤ ዐጥንቴም በትኵሳት ነደደ። 31 በገናዬ ለሐዘን፣ እንቢልታዬም ለልቅሶ ተቃኝቷል። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.