ኢዮብ 3 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምኢዮብ ይናገራል 1 ከዚህ በኋላ፣ ኢዮብ አፉን ከፍቶ የተወለደበትን ቀን ረገመ፤ 2 ኢዮብም እንዲህ አለ፤ 3 “የተወለድሁበት ቀን ይጥፋ፤ ‘ወንድ ልጅ ተፀነሰ’ የተባለበት ሌሊት። 4 ያ ቀን ጨለማ ይሁን፤ እግዚአብሔር ከላይ አይመልከተው፤ ብርሃንም አይብራበት። 5 ጨለማና የሞት ጥላ ይውረሱት፤ ደመናም በላዩ ላይ ይረፍ፤ ብርሃኑን ጽልመት ይዋጠው። 6 ያ ሌሊት በድቅድቅ ጨለማ ይያዝ፤ ከዓመቱ ቀናት ጋራ አይቈጠር፤ ከወራቱ በአንዱም ውስጥ አይግባ። 7 ያ ሌሊት መካን ይሁን፤ እልልታም አይሰማበት። 8 ሌዋታንን ለማነሣሣት የተዘጋጁ፤ ቀንንም የሚረግሙ ያን ቀን ይርገሙት። 9 አጥቢያ ኮከቦቹ ይጨልሙ፤ ብርሃንን እየጠበቀ ይጣ፤ የንጋት ጮራ ሲፈነጥቅ አይይ። 10 መከራን ከዐይኔ ይሰውር ዘንድ፣ የእናቴን ማሕፀን ደጅ በላዬ አልዘጋምና። 11 “ምነው ገና ስወለድ በጠፋሁ! ምነው ከማሕፀን ስወጣ በሞትሁ! 12 የሚቀበሉኝ ጕልበቶች፤ የሚያጠቡኝ ጡቶች ለምን ተገኙ? 13 ይህን ጊዜ በሰላም በተኛሁ፣ አንቀላፍቼም ባረፍሁ ነበር፤ 14 አሁን ፈርሶ የሚታየውን ስፍራ ለራሳቸው ካሠሩት፣ ከምድር ነገሥታትና ከአማካሪዎች ጋራ፣ 15 ቤታቸውን በብር ከሞሉ፣ ወርቅም ከነበራቸው ገዦች ጋራ ባረፍሁ ነበር። 16 ወይም እንደ ተቀበረ ጭንጋፍ፣ ብርሃንም እንዳላየ ሕፃን በሆንሁ ነበር። 17 በዚያ ክፉዎች ማወካቸውን ይተዋሉ፤ ደካሞችም በዚያ ያርፋሉ፤ 18 ምርኮኞች እንደ ልባቸው ይቀመጣሉ፤ ከእንግዲህም የአስጨናቂዎቻቸውን ጩኸት አይሰሙም። 19 ትንሹም ትልቁም በዚያ ይገኛል፤ ባሪያው ከጌታው ነጻ ወጥቷል። 20 “በመከራ ላሉት ብርሃን፣ ነፍሳቸው ለተማረረች ሕይወት ለምን ተሰጠ? 21 ሞትን በጕጕት ለሚጠብቁና ለማያገኙት፣ ከተሰወረ ሀብት ይልቅ ለሚሹት፣ 22 ወደ መቃብር ሲቃረቡ ደስ እያላቸው፣ በሐሤት ለሚሞሉ ሕይወት ለምን ተሰጠ? 23 መንገዱ ለተሰወረበት ሰው፤ እግዚአብሔርም በዐጥር ላጠረው፣ ሕይወት ለምን ተሰጠ? 24 ትካዜ ምግብ ሆኖኛልና፤ የሥቃይ ጩኸቴም እንደ ውሃ ይፈስሳል። 25 የፈራሁት ነገር መጥቶብኛል፤ የደነገጥሁበትም ደርሶብኛል። 26 ሰላም የለኝም፤ ርጋታም የለኝም፤ ሁከት እንጂ ዕረፍት የለኝም።” |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.