Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ኢዮብ 29 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም

1 ኢዮብም እንዲህ ሲል ንግግሩን ቀጠለ፤

2 “በእግዚአብሔር የተጠበቅሁበትን ዘመን፣ ያለፈውንም ወራት ምንኛ ተመኘሁ!

3 ያን ጊዜ መብራቱ በራሴ ላይ ይበራ ነበር፤ በብርሃኑም በጨለማ ውስጥ ዐልፌ እሄድ ነበር፤

4 እኔም ብርቱ ነበርሁ፤ የእግዚአብሔርም ወዳጅነት ቤቴን ይባርክ ነበር፤

5 ሁሉን ቻይ አምላክ ከእኔ ጋራ ነበረ፤ ልጆቼም በዙሪያዬ ነበሩ፤

6 መንገዴ በቅቤ የራሰ ነበር፤ ዐለቱም የወይራ ዘይት ያመነጭልኝ ነበር።

7 “ወደ ከተማዪቱ በር ብቅ ባልሁ ጊዜ፣ በአደባባይዋም በወንበር በተቀመጥሁ ጊዜ፣

8 ጐበዛዝት አይተውኝ ገለል ይሉ፣ ሽማግሌዎችም ተነሥተው ይቆሙ ነበር።

9 የሰፈሩ ታላላቅ ሰዎች ከመናገር ይቈጠቡ፣ እጃቸውንም በአፋቸው ላይ ይጭኑ ነበር፤

10 የመኳንንት ድምፅ ጸጥ ይል፣ ምላሳቸውም ከላንቃቸው ጋራ ይጣበቅ ነበር፤

11 የሰሙኝ ሁሉ ያሞጋግሱኝ፣ ያዩኝም ያመሰግኑኝ ነበር፤

12 ለርዳታ የሚጮኸውን ችግረኛ፣ ድኻ አደጉንም ታድጌአለሁና።

13 በሞት አፋፍ ላይ የነበረ መርቆኛል፤ የመበለቲቱንም ልብ አሳርፌአለሁ።

14 ጽድቅን እንደ ልብስ ለበስሁ፤ ፍትሕም መጐናጸፊያዬና ጥምጥሜ ነበር።

15 ለዕውራን ዐይን፣ ለዐንካሶችም እግር ነበርሁ።

16 ለድኾች አባት፣ ለባይተዋሩ ተሟጋች ነበርሁ።

17 የኀጢአተኛውን ክራንቻ ሰበርሁ፤ የነጠቀውንም ከጥርሶቹ አስጣልሁ።

18 “እኔም በልቤ እንዲህ አልሁ፤ ‘ዘመኔ እንደ አሸዋ በዝቶ፣ በቤቴ ተደላድዬ እሞታለሁ፤

19 ሥሬ ወደ ውሃ ይዘረጋል፤ ጠልም በቅርንጫፌ ላይ ያድራል፤

20 ክብሬ በውስጤ አዲስ እንደ ሆነ፣ ቀስትም በእጄ እንደ በረታ ይኖራል።’

21 “ሰዎች ምክሬን በጸጥታ በመጠባበቅ፣ በጕጕት አደመጡኝ።

22 እኔ ከተናገርሁ በኋላ፣ የሚናገር ሰው አልነበረም፤ ቃሌም እየተንጠባጠበ በጆሯቸው ይገባ ነበር።

23 ዝናብ እንደሚጠብቅ ሰው ጠበቁኝ፤ ቃሌንም እንደ በልግ ዝናብ ጠጡ፤

24 በሣቅሁላቸው ጊዜ እውነት አልመሰላቸውም፤ የፊቴም ብርሃን ብርቃቸው ነበር።

25 መንገድ መርጬላቸው አለቃቸው ሆኜ ተቀመጥሁ፤ በሰራዊትም መካከል እንዳለ ንጉሥ ኖርሁ፤ ሐዘንተኞችንም እንደሚያጽናና ነበርሁ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告