Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ኢዮብ 27 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም

1 ኢዮብም እንዲህ ሲል ንግግሩን ቀጠለ፤

2 “ፍትሕ የነሣኝ ሕያው እግዚአብሔርን! ነፍሴንም መራራ ያደረጋት፣ ሁሉን ቻይ አምላክን!

3 በውስጤ የሕይወት እስትንፋስ፣ በአፍንጫዬም ውስጥ የእግዚአብሔር መንፈስ እስካለ ድረስ፣

4 ከንፈሬ ኀጢአትን አትናገርም፤ አንደበቴም ሽንገላ አይወጣውም።

5 እናንተን እንደ ቅኖች መቍጠር፣ የማላደርገው ነገር ነው፤ ጨዋነቴንም እስክሞት ድረስ አልጥልም።

6 ጽድቄን አጥብቄ እይዛለሁ፤ አልለቀውምም፤ በዘመኔም ሁሉ ኅሊናዬ አይወቅሠኝም።

7 “ጠላቴ እንደ በደለኛ፣ ባላንጣዬም እንደ ክፉ ይሁን።

8 እግዚአብሔር ሲያስወግደው፣ ነፍሱንም ሲወስድበት ዐመፀኛ ምን ተስፋ አለው?

9 በውኑ መከራ በገጠመው ጊዜ፣ እግዚአብሔር ጩኸቱን ይሰማልን?

10 ሁሉን ቻይ አምላክ ደስ ይለዋልን? ዘወትርስ እግዚአብሔርን ይጠራልን?

11 “ስለ እግዚአብሔር ክንድ አስተምራችኋለሁ፤ የሁሉን ቻዩንም አምላክ ዕቅድ አልሸሽግም።

12 ሁላችሁ ይህን አይታችኋል፤ ታዲያ፣ ይህ ከንቱ ንግግር ምንድን ነው?

13 “እግዚአብሔር ለክፉው ሰው የመደበው ዕድል ፈንታ፣ ግፈኛም ሁሉን ቻይ አምላክ የሚቀበለው ቅርስ ይህ ነው፦

14 ልጆቹ የቱንም ያህል ቢበዙም ለሰይፍ ይዳረጋሉ፤ ዘሩም ጠግቦ አያድርም።

15 የተረፉለትም በመቅሠፍት ዐልቀው ይቀበራሉ፤ መበለቶቻቸውም አያለቅሱላቸውም።

16 ብርን እንደ ዐፈር ቢከምር፣ ልብስንም እንደ ሸክላ ጭቃ ቢያከማች፣

17 እርሱ ያከማቸውን ጻድቃን ይለብሱታል፤ ብሩንም ንጹሓን ይከፋፈሉታል።

18 የሚሠራው ቤት እንደ ሸረሪት ድር፣ እህል ጠባቂም እንደ ቀለሰው መጠለያ ነው።

19 ሀብታም ሆኖ ይተኛል፤ ዘለቄታ ግን የለውም፤ ዐይኑን በገለጠ ጊዜ ሀብቱ ሁሉ በቦታው የለም።

20 ድንጋጤ እንደ ጐርፍ ድንገት ያጥለቀልቀዋል፤ ዐውሎ ነፋስም በሌሊት ይዞት ይሄዳል።

21 የምሥራቅ ነፋስ ይወስደዋል፤ እርሱም አይገኝም፤ ከስፍራውም ይጠርገዋል።

22 ከነፋሱ ብርታት ለማምለጥ ይሮጣል፤ ነገር ግን እየተወረወረ ያለ ርኅራኄ ይደርስበታል፤

23 እጁንም እያጨበጨበ ያሾፍበታል፤ በፉጨትም ከስፍራው ያሽቀነጥረዋል።”

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告