ኢዮብ 26 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምኢዮብ 1 ኢዮብም እንዲህ ሲል መለሰ፤ 2 “ኀይል የሌለውን ምንኛ ረዳኸው! ደካማውንስ ምንኛ አዳንኸው! 3 ጥበብ የሌለውን ምንኛ መከርኸው! ታላቅ ዕውቀትንስ ምንኛ ገለጥህለት! 4 ይህን ቃል እንድትናገር የረዳህ ማን ነው? የማንስ መንፈስ በአንደበትህ ተጠቀመ? 5 “ከውሆችና በውስጣቸው ከሚኖሩ በታች ያሉ፣ የሙታን መንፈስ በጭንቅ ላይ ናቸው። 6 ሲኦል በአምላክ ፊት ዕራቍቷን ናት፤ የጥፋትንም ስፍራ የሚጋርድ የለም። 7 የሰሜንን ሰማይ በሕዋው ላይ ዘረጋው፤ ምድርንም እንዲያው በባዶው ላይ አንጠለጠላት። 8 ውሆችን በደመናዎቹ ይጠቀልላል፤ ክብደታቸውም ደመናዎቹን አይሸነቍርም። 9 ደመናዎቹን በላዩ ዘርግቶ፣ የሙሉውን ጨረቃ ፊት ይጋርዳል። 10 ለብርሃንና ለጨለማ ድንበር ይሆን ዘንድ፣ በውሆች ላይ የአድማስ ክበብ አበጀ። 11 የሰማይ ምሰሶዎች ይንቀጠቀጣሉ፤ በተግሣጹም ይደነግጣሉ። 12 በኀይሉ ባሕርን ያናውጣል፤ በጥበቡም ረዓብን ይቈራርጣል። 13 በእስትንፋሱ ሰማያትን አጠራ፤ እጁም ተወርዋሪውን እባብ ወጋች። 14 እነዚህ የሥራው ዳር ዳር ናቸው፤ ስለ እርሱ የሰማነው ምንኛ አነስተኛ ነው! የኀይሉንስ ነጐድጓድ ማን ሊያስተውል ይችላል?” |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.