ኢዮብ 23 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምኢዮብ 1 ኢዮብም እንዲህ ሲል መለሰ፤ 2 “ዛሬም ሐዘኔ መራራ ነው፤ እያቃሰትሁ እንኳ እጁ በላዬ ከብዳለች። 3 እርሱን የት እንደማገኘው ባወቅሁ፤ ወደ መኖሪያውም መሄድ በቻልሁ! 4 ጕዳዬን በፊቱ አቀርብ ነበር፤ አፌንም በሙግት እሞላው ነበር። 5 የሚመልስልኝ ቃል ምን እንደ ሆነ ባወቅሁ ነበር፤ የሚለኝንም ባስተዋልሁ ነበር። 6 በታላቅ ኀይሉ ከእኔ ጋራ ይሟገት ይሆን? አይደለም፤ ይልቁን ያደምጠኛል። 7 ቅን ሰው ጕዳዩን በርሱ ፊት ያቀርባል፤ እኔም ከፈራጄ ለዘላለም ነጻ እሆናለሁ። 8 “ዳሩ ግን ወደ ምሥራቅ ብሄድ፣ በዚያ የለም፤ ወደ ምዕራብም ብሄድ፣ እርሱን አላገኘውም፤ 9 በሰሜን እየሠራ ሳለ አላየውም፤ ወደ ደቡብ በሚዞርበት ጊዜ ደብዛው አይገኝም። 10 ግን እኔ የምሄድበትን መንገድ ያውቃል፤ ከፈተነኝም በኋላ እንደ ወርቅ እወጣለሁ። 11 እግሮቼ ርምጃውን በጥብቅ ተከታትለዋል፤ ፈቀቅ ሳልል መንገዱን ጠብቄአለሁ። 12 ከአፉ ከወጣው ትእዛዝ አልራቅሁም፣ የአንደበቱን ቃል ከዕለት እንጀራዬ አብልጬ ይዣለሁ። 13 “እርሱ ግን ራሱን ችሎ ብቻውን የሚኖር ነው፤ የሚቋቋመውስ ማን ነው? እርሱ የፈቀደውን ያደርጋል። 14 በእኔ ላይ የወሰነውን ይፈጽማል፤ ይህን የመሰለ ዕቅድም ገና ብዙ አለው። 15 በፊቱ የደነገጥሁትም ለዚህ ነው፤ ይህን ሁሉ ሳስብ እፈራለሁ። 16 እግዚአብሔር ልቤን አባባው፤ ሁሉን ቻይ አምላክ አስደነገጠኝ። 17 ይህም ሆኖ ሳለ ጨለማው፣ ፊቴንም የጋረደው ጽልመት ልሳኔን አልዘጋውም። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.