Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ኢዮብ 22 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


ኤልፋዝ

1 ቴማናዊውም ኤልፋዝ እንዲህ ሲል መለሰ፤

2 “ሰው እግዚአብሔርን ሊጠቅም ይችላልን? ጠቢብ እንኳ ቢሆን ምን ይጠቅመዋል?

3 አንተ ጻድቅ ብትሆን ሁሉን ቻዩን አምላክ ምን ደስ ታሠኘዋለህ? መንገድህ ያለ ነቀፋ ቢሆንስ የሚተርፈው ምንድን ነው?

4 “እርሱ የሚገሥጽህ፣ ፍርድ ቤትም የሚያቀርብህ ስለምትፈራው ነውን?

5 ክፋትህ ታላቅ፣ ኀጢአትህ ፍጻሜ የሌለው አይደለምን?

6 ያለ አንዳች ምክንያት ከወንድሞችህ መያዣ ወስደሃል፤ ሰዎችን ገፍፈህ፣ ያለ ልብስ ዕራቍታቸውን አስቀርተሃል።

7 የዛሉትን ውሃ አላጠጣህም፤ የተራቡትንም ምግብ ከልክለሃል።

8 ባለርስትና ኀያል፣ በርሱም የምትኖር ክቡር ሰው ብትሆንም፣

9 መበለቶችን ባዶ እጃቸውን ሰድደሃል፤ የድኻ አደጎችንም ክንድ ሰብረሃል።

10 ድንገተኛ አደጋ ያናወጠህ፣ ወጥመድም ዙሪያህን የከበበህ ለዚህ ነው።

11 እንዳታይ ጨለማ የሆነብህ፣ ጐርፍም ያጥለቀለቀህ ለዚህ ነው።

12 “እግዚአብሔር ከፍ ባለው ሰማይ የሚኖር አይደለምን? በሩቅ ከፍታ ያሉትን ከዋክብት ያያል!

13 ይህም ሆኖ ሳለ እንዲህ አልህ፤ ‘እግዚአብሔር ምን ያውቃል? በእንዲህ ያለ ጨለማ ውስጥስ ይፈርዳልን?

14 በሰማይ ክበብ ላይ ሲራመድ፣ እንዳያየን ጥቅጥቅ ያለ ደመና ይሸፍነዋል።’

15 ኀጢአተኞች በሄዱባት፣ በጥንቷ መንገድ እንደ ተመላለስህ ትቀራለህን?

16 ጊዜያቸው ሳይደርስ ተነጠቁ፤ መሠረታቸውም በጐርፍ ተወሰደ።

17 እግዚአብሔርንም ‘አትድረስብን! ሁሉን ቻይ አምላክም ምን ያደርግልናል?’ አሉ።

18 ቤታቸውን በመልካም ነገር የሞላው ግን እርሱ ነው፤ ስለዚህ ከኀጢአተኞች ምድር እርቃለሁ።

19 ጻድቃንም የእነዚያን ጥፋት አይተው ይደሰታሉ፤ ንጹሓንም እንዲህ ብለው ያፌዙባቸዋል፤

20 ‘በርግጥ ጠላቶቻችን ጠፍተዋል፤ ሀብታቸውም በእሳት ተበልቷል።’

21 “ለእግዚአብሔር ተገዛ፤ ከርሱም ጋራ ሰላም ይኑርህ፤ በረከትም ታገኛለህ።

22 ምክርን ከአፉ ተቀበል፤ ቃሉንም በልብህ አኑር።

23 ወደ ሁሉን ቻይ አምላክ ብትመለስ ትጠገናለህ፤ ክፋትን ከድንኳንህ ብታርቅ፣

24 የወርቅህን አንኳር ትቢያ ላይ፣ የኦፊር ወርቅህንም ጥልቅ ሸለቆ ውስጥ ብትጥለው፣

25 ሁሉን ቻዩ አምላክ ወርቅ ይሆንልሃል፤ ምርጥ ብር ይሆንልሃል።

26 በዚያ ጊዜ በሁሉን ቻይ አምላክ ደስ ይልሃል፤ ፊትህንም ወደ እግዚአብሔር ታቀናለህ።

27 ወደ እርሱ ትጸልያለህ፤ እርሱም ይሰማሃል፤ አንተም ስእለትህን ትሰጣለህ።

28 ያሰብኸው ይከናወንልሃል፤ በመንገድህም ላይ ብርሃን ይበራል።

29 ሰዎች ቢዋረዱና አንተ፣ ‘ከፍ አድርጋቸው’ ብትል፣ እርሱ ዝቅ ያሉትን ያድናል፤

30 በጎ ያልሆነውን ሰው እንኳ፣ ከአንተ እጅ ንጽሕና የተነሣ ያድነዋል።”

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告