Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ኢዮብ 21 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


ኢዮብ

1 ኢዮብም እንዲህ ሲል መለሰ፤

2 “ቃሌን በጥንቃቄ ስሙ፤ የምታጽናኑኝም በዚህ ይሁን፤

3 አኔ ስናገር ታገሡኝ፤ ከተናገርሁ በኋላ፣ መሣለቅ ትችላላችሁ።

4 “በውኑ ቅርታዬ በሰው ላይ ነውን? ትዕግሥት ማጣትስ አይገባኝምን?

5 ተመልከቱኝና ተገረሙ፤ አፋችሁን በእጃችሁ ለጕሙ።

6 ስለዚህ ነገር ባሰብሁ ቍጥር እደነግጣለሁ፤ ሰውነቴም በፍርሀት ይንቀጠቀጣል።

7 ኀጢአተኞች ለምን በሕይወት ይኖራሉ? ለምን ለእርጅና ይበቃሉ? ለምንስ እያየሉ ይሄዳሉ?

8 ዘራቸው በዐይናቸው ፊት፣ ልጆቻቸውም በዙሪያቸው ጸንተው ሲኖሩ ያያሉ፤

9 ቤታቸው ያለ ሥጋት በሰላም ይኖራል፤ የእግዚአብሔርም በትር የለባቸውም።

10 ኰርማቸው ዘሩ በከንቱ አይወድቅም፤ ያስረግዛል፤ ላማቸውም ሳትጨነግፍ ትወልዳለች።

11 ልጆቻቸውን እንደ በግ መንጋ ያሰማራሉ፤ ሕፃናታቸውም ይቦርቃሉ።

12 በከበሮና በክራር ይዘፍናሉ፤ በዋሽንትም ድምፅ ይፈነጫሉ።

13 ዕድሜያቸውን በተድላ ያሳልፋሉ፤ በሰላምም ወደ መቃብር ይወርዳሉ።

14 እግዚአብሔርንም እንዲህ ይሉታል፤ ‘አትድረስብን! መንገድህንም ማወቅ አንፈልግም።

15 እናገለግለው ዘንድ፣ ሁሉን ቻይ አምላክ ማን ነው? ወደ እርሱ ብንጸልይስ ምን እናገኛለን?’

16 ይሁንና ብልጽግናቸው በእጃቸው አይደለም፤ ከኀጢአተኞች ምክር እርቃለሁ።

17 “የኀጢአተኞች መብራት የጠፋው ስንት ጊዜ ነው? የእግዚአብሔር ቍጣ መከራ የመጣባቸው፣ መቅሠፍትም የደረሰባቸው ስንት ጊዜ ነው?

18 በነፋስ ፊት እንዳለ ገለባ፣ በዐውሎ ነፋስም እንደ ተወሰደ ዕብቅ የሆኑት ስንት ጊዜ ነው?

19 እናንተ፣ ‘እግዚአብሔር የሰውን ቅጣት ለልጆቹ ያከማቻል’ ትላላችሁ፤ ነገር ግን ያውቀው ዘንድ ለሰውየው ለራሱ ይክፈለው፤

20 ዐይኖቹ የራሱን ውድቀት ይዩ፤ ከሁሉን ቻይ አምላክ ቍጣ ይጠጣ።

21 ሰው ወራቱ በተገባደደ ጊዜ፣ ለቀሪ ቤተ ሰቡ ምን ይገድደዋል?

22 “ከፍ ባሉት ላይ ለሚፈርድ አምላክ፣ ዕውቀትን ሊያስተምረው የሚችል አለን?

23 አንድ ሰው በፍጹም ተድላ ደስታ እየኖረ፣ በሙሉ ብርታቱም እያለ ይሞታል፤

24 ሰውነቱ በምቾት፣ ዐጥንቱም በሥብ ተሞልቶ እያለ በሞት ይለያል።

25 ሌላው ሰው ደግሞ አንዳች መልካም ነገር ሳያይ፣ በተመረረች ነፍስ ይሞታል፤

26 ሁለቱም በዐፈር ውስጥ አንድ ላይ ይተኛሉ፤ ትልም ይወርሳቸዋል።

27 “እነሆ፣ ምክራችሁን፣ በእኔ ላይ ያሤራችሁትንም ተረድቻለሁ።

28 እናንተ፣ ‘የትልቁ ሰው ቤት፣ ኀጢአተኛውም የኖረበት ድንኳን የት አለ?’ አላችሁ፤

29 መንገደኞችን አልጠየቃችሁምን? የነገሯችሁንስ ነገር በጥሞና አላዳመጣችሁምን?

30 ክፉ ሰው በመቅሠፍት ቀን እንደሚጠበቅ፣ በቍጣም ቀን እንደሚተርፍ አታውቁምን?

31 ተግባሩን ፊት ለፊት የሚነግረው ማን ነው? የእጁንስ ማን ይሰጠዋል?

32 ወደ መቃብር ይወስዱታል፤ ለመቃብሩም ጠባቂ ይደረግለታል።

33 የሸለቈው ዐፈር ምቹ ይሆንለታል፤ ሰው ሁሉ ይከተለዋል፤ ስፍር ቍጥር የሌለው ሕዝብ በፊቱ ይሄዳል።

34 “መልሳችሁ ከሐሰት በቀር ሌላ አይገኝበትም! ታዲያ፣ በማይረባ ነገር እንዴት ልታጽናኑኝ ትችላላችሁ?”

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告