ኢዮብ 20 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምሶፋር 1 ናዕማታዊውም ሶፋር እንዲህ ሲል መለሰ፤ 2 “እጅግ ታውኬአለሁና፣ ሐሳቤ መልስ እንድሰጥ ይጐተጕተኛል። 3 የሚያቃልለኝን ንግግር ሰምቼአለሁ፤ መልስም እሰጥ ዘንድ ማስተዋሌ ገፋፋኝ። 4 “ሰው በምድር ላይ ከተቀመጠ ጊዜ ጀምሮ፣ ከጥንቱ እንዴት እንደ ነበረ ታውቃለህን? 5 የኀጢአተኞች መፈንጨት ለዐጭር ጊዜ፣ የክፉዎችም ደስታ ለቅጽበት መሆኑን አታውቅምን? 6 እስከ ሰማይ ከፍ ከፍ ቢልም፣ ዐናቱም ደመናትን ቢነካ፣ 7 እንደ ኵበት ለዘላለም ይጠፋል፤ ቀድሞ ያዩትም፣ ‘የት ገባ?’ ይላሉ። 8 እንደ ሕልም በርሮ ይጠፋል፤ አይገኝምም፤ እንደ ሌሊትም ራእይ በቅጽበት ያልፋል። 9 ቀድሞ ያየው ዐይን ዳግመኛ አያየውም፤ የነበረበትም ቦታ ከእንግዲህ አይመለከተውም። 10 ልጆቹ ለድኾች ካሳ መክፈል አለባቸው፤ እጆቹም ሀብቱን መልሰው መስጠት ይገባቸዋል። 11 ዐጥንቱን የሞላው የወጣትነት ብርታት፣ ከርሱ ጋራ በዐፈር ውስጥ ይተኛል። 12 “ክፋት በአፉ ውስጥ ቢጣፍጥ፣ ከምላሱም በታች ቢደብቀው፣ 13 አውጥቶ ለመጣል እየሳሳ፣ በአፉ ውስጥ ቢያቈየው፣ 14 ምግቡ በሆዱ ውስጥ ይመርራል፤ በውስጡም እንደ እባብ መርዝ ይሆናል። 15 የዋጠውን ሀብት ይተፋል፤ እግዚአብሔርም መልሶ ከሆዱ ያወጣዋል። 16 የእባብ መርዝ ይጠባል፤ የእፉኝትም ምላስ ይገድለዋል። 17 ማርና ቅቤ በሚያፈስሱ ጅረቶች፣ በወንዞችም አይደሰትም። 18 የለፋበትን ሳይበላው ይመልሳል፤ ከንግዱም ባገኘው ትርፍ አይደሰትም፤ 19 ድኾችን በመጨቈን ባዶ አስቀርቷቸዋልና፣ ያልሠራውንም ቤት ነጥቋል። 20 “ክፉ ምኞቱ ዕረፍት አይሰጠውም ሀብቱም ሊያድነው አይችልም። 21 ያለውን አሟጥጦ ስለሚበላ፣ ዘላቂ ብልጽግና አይኖረውም። 22 በተድላ መካከል እያለ ጕስቍልና ይመጣበታል፤ በከባድ መከራም ይዋጣል። 23 ሆዱን በሞላ ጊዜ፣ እግዚአብሔር የሚነድድ ቍጣውን ይሰድበታል፤ መዓቱንም ያወርድበታል። 24 ከብረት መሣሪያ ቢሸሽም፣ የናስ ቀስት ይወጋዋል። 25 ቀስቱን ከጀርባው፣ የሚያብለጨልጨውንም ጫፍ ከጕበቱ ይመዝዛል፤ ፍርሀትም ይይዘዋል፤ 26 ሀብቱ ለድቅድቅ ጨለማ ተዳርጓል፤ ሰው ባላራገበው እሳት ይበላል፤ በድንኳኑም ውስጥ የተረፈውን ይልሳል። 27 ሰማያት ኀጢአቱን ይገልጡበታል፤ ምድርም ትነሣበታለች፤ 28 በእግዚአብሔር የቍጣ ቀን ቤቱን ጐርፍ፣ መኖሪያውንም ወራጅ ውሃ ይወስድበታል። 29 እግዚአብሔር ለክፉ ሰዎች የወሰነው ዕድል ፈንታ፣ ከአምላክም ዘንድ የተመደበላቸው ቋሚ ቅርስ ይህ ነው።” |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.