Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ኢዮብ 2 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


ሁለተኛው የኢዮብ ፈተና

1 በሌላ ቀን ደግሞ፤ መላእክት በእግዚአብሔር ፊት ለመቆም መጡ። ሰይጣንም ከእነርሱ ጋራ በእግዚአብሔር ፊት ሊቆም መጣ።

2 እግዚአብሔር ሰይጣንን፣ “ከወዴት መጣህ?” አለው። ሰይጣንም፣ “በምድር ሁሉ ዞርሁ፤ ወዲያና ወዲህም ተመላለስሁባት” ብሎ ለእግዚአብሔር መለሰ።

3 እግዚአብሔርም ሰይጣንን፣ “አገልጋዬን ኢዮብን ተመለከትኸውን? በምድር ላይ እንደ እርሱ ነቀፋ የሌለበት፣ ቅን፣ እግዚአብሔርን የሚፈራና ከክፋት የራቀ ሰው የለም፤ ያለ ምክንያት እንዳጠፋው ብትወተውተኝም፣ ይኸው ፍጹምነቱን እንደ ጠበቀ ነው” አለው።

4 ሰይጣንም እንዲህ ሲል ለእግዚአብሔር መለሰ፤ “ ‘ቍርበት ስለ ቍርበት ነው’ እንዲሉ ሰው ለሕይወቱ ሲል ያለውን ሁሉ ይሰጣል፤

5 እስኪ እጅህን ዘርግተህ ዐጥንቱንና ሥጋውን ዳስስ፤ በርግጥ ፊት ለፊት ይሰድብሃል።”

6 እግዚአብሔርም ሰይጣንን፣ “እነሆ፤ እርሱ በእጅህ ነው፤ ሕይወቱን ግን እንዳትነካ” አለው።

7 ከዚህ በኋላ ሰይጣን ከእግዚአብሔር ፊት ወጥቶ ሄደ፤ ኢዮብንም ከእግር ጥፍሩ እስከ ራስ ጠጕሩ በክፉ ቍስል መታው።

8 ኢዮብም ገላውን ለማከክ ገል ወሰደ፤ በዐመድም ላይ ተቀመጠ።

9 ሚስቱም፣ “አሁንም ታማኝነትህን አልተውህምን? ይልቁን እግዚአብሔርን ርገምና ሙት!” አለችው።

10 እርሱም፣ “አነጋገርሽ እንደ ሞኝ ሴት ነው፤ መልካሙን ነገር ከእግዚአብሔር ዘንድ ተቀበልን፤ ክፉውንስ አንቀበልምን? አላት።” በዚህ ሁሉ፣ ኢዮብ በንግግሩ አልበደለም።


ሦስቱ የኢዮብ ወዳጆች

11 ሦስቱ የኢዮብ ወዳጆች ቴማናዊው ኤልፋዝ፣ ሹሐዊው በልዳዶስ፣ ናዕማታዊውም ሶፋር በኢዮብ ላይ የደረሰውን መከራ ሁሉ በሰሙ ጊዜ፣ ሄደው ሊያስተዛዝኑትና ሊያጽናኑት በመስማማት ከየመኖሪያቸው በአንድነት መጡ።

12 እነርሱም ከሩቅ ሆነው ሲመለከቱት እርሱ መሆኑን ሊለዩ አልቻሉም፤ በዚህ ጊዜ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ፤ ልብሳቸውንም ቀድደው በራሳቸው ላይ ትቢያ ነሰነሱ።

13 ሰባት ቀንና ሰባት ሌሊት ከርሱ ጋራ መሬት ላይ ተቀመጡ፤ ሥቃዩ ታላቅ መሆኑንም ስለ ተረዱ፣ አንዳች ቃል የተናገረው አልነበረም።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告