ኢዮብ 17 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም1 መንፈሴ ደክሟል፣ ዘመኔ ዐጥሯል፤ መቃብርም ተዘጋጅቶልኛል። 2 አላጋጮች ከብበውኛል፤ ትኵረቴም ትንኰሳቸው ላይ ነው። 3 “አምላክ ሆይ፤ አንተ ተያዥ ሁነኝ፤ ከአንተ ሌላ ዋስ የሚሆነኝ ማን አለ? 4 እንዳያስተውሉ ልባቸውን ይዘሃል፤ ስለዚህ ድል አትሰጣቸውም። 5 ለጥቅም ሲል ወዳጁን የሚያወግዝ፣ የልጆቹ ዐይን ይታወራል። 6 “አምላክ ለሰው ሁሉ መተረቻ፣ ፊቱ ላይ የሚተፋበት ሰውም አደረገኝ። 7 ዐይኔ ከሐዘን የተነሣ ፈዘዘ፤ መላ አካሌም እንደ ጥላ ሆነ። 8 ቅኖች በዚህ ነገር ይደነግጣሉ፤ ንጹሓንም በዐመፀኞች ላይ ይነሣሉ። 9 ጻድቃን ግን በያዙት መንገድ ይጸናሉ፤ ንጹሕ እጅ ያላቸውም እየበረቱ ይሄዳሉ። 10 “ነገር ግን እናንተ ሁላችሁ፣ እስኪ ተመልሳችሁ እንደ ገና ሞክሩ! ከመካከላችሁ አንድም ጠቢብ አላገኝም። 11 ዕድሜዬ ዐለቀ፤ ዕቅዴም ከሸፈ፤ የልቤም ሐሳብ ከንቱ ሆነ። 12 እነዚህ ሰዎች ሌሊቱን ወደ ቀን ይለውጣሉ፤ ጨልሞም እያዩ፣ ‘ብርሃን ቀርቧል’ ይላሉ። 13 ተስፋ የማደርገው ቤት መቃብር ብቻ ከሆነ፣ መኝታዬንም በጨለማ ካነጠፍሁ፣ 14 መበስበስን፣ ‘አንተ አባቴ ነህ፤’ ትልንም፣ ‘አንቺ እናቴ’ ወይም ‘እኅቴ ነሽ’ ካልሁ፣ 15 ታዲያ፣ የእኔ ተስፋ ወዴት ነው? ተስፋዬን የሚያይልኝስ ማን ነው? 16 ወደ ሞት ደጅ ይወርዳልን? ዐብረንስ ወደ ትቢያ እንሄዳለንን?” |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.