ኢዮብ 16 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምኢዮብ 1 ኢዮብም እንዲህ ሲል መለሰ፤ 2 “ይህን የሚመስል ብዙ ነገር ሰምቻለሁ፤ እናንተ ሁላችሁ የምታስጨንቁ አጽናኞች ናችሁ። 3 ይህ ከንቱ ንግግር አያልቅምን? ትለፈልፍ ዘንድ የሚገፋፋህ ምንድን ነው? 4 እናንተ በእኔ ስፍራ ብትሆኑ ኖሮ፣ እኔም እንደ እናንተ መናገር እችል ነበር፤ ቃላት አሳክቼ በመናገር፣ በእናንተ ላይ ራሴን መነቅነቅ በቻልሁ ነበር። 5 ይልቁንም አንደበቴ ባበረታታችሁ፣ የከንፈሬም ማጽናናት ባሳረፋችሁ ነበር። 6 “ብናገር ሕመሜ አይሻለኝም፤ ዝም ብልም አይተወኝም። 7 እግዚአብሔር ሆይ አሁንስ አድክመኸኛል፤ ወገኖቼንም ሁሉ አጥፍተሃል። 8 ጭምትርትር ያደረግኸኝ ምስክር ሆኖብኛል፣ ዐጥንቴን ያወጣው ክሳቴም ያጋልጠኛል። 9 በቍጣው ሰነጠቀኝ፤ በጥላቻው አስጨነቀኝ፣ ጥርሱን ነከሰብኝ፤ ባላጋራዬ ክፉ ዐይኑን ተከለብኝ። 10 ሰዎች በፌዝ አፋቸውን ከፈቱብኝ፤ በንቀት ጕንጬን ጠፈጠፉኝ፤ በአንድነትም በላዬ ተሰበሰቡ። 11 እግዚአብሔር ለክፉዎች አሳልፎ ሰጠኝ፤ በጠማሞችም እጅ ጣለኝ። 12 በሰላም እኖር ነበር፤ እርሱ ግን ሰባበረኝ፤ ዐንገቴን ይዞ አደቀቀኝ፤ ማነጣጠሪያ ዒላማው አደረገኝ፤ 13 የርሱ ቀስተኞች ከበቡኝ፤ ያለ ርኅራኄ ኵላሊቴን ይበጣጥሳል፤ ሐሞቴን መሬት ላይ ያፈስሳል። 14 ደጋግሞ ይቀጠቅጠኛል፤ እንደ ጦረኛም ተንደርድሮ ይመጣብኛል። 15 “በቈዳዬ ላይ ማቅ ሰፍቻለሁ፤ ቀንዴን በዐፈር ውስጥ ቀብሬአለሁ። 16 ፊቴ ከልቅሶ የተነሣ ቀልቷል፤ ጨለማም በዐይኖቼ ቆብ ላይ ዐርፏል፤ 17 ነገር ግን በእጄ ዐመፅ አይገኝም፤ ጸሎቴም ንጹሕ ነው። 18 “ምድር ሆይ፤ ደሜን አትሸፍኚ፤ ጩኸቴም ማረፊያ አያግኝ! 19 አሁን እንኳ ምስክሬ በሰማይ አለ፤ ጠበቃዬም በላይ በአርያም ይገኛል። 20 ወዳጆቼ በንቀት ቢመለከቱኝም፣ ዐይኔ ወደ እግዚአብሔር ያነባል። 21 ሰው ለወዳጁ እንደሚማልድ፣ በእግዚአብሔር ፊት የሚማልድ ሰው ምነው በተገኘ! 22 “ከጥቂት ዓመታት በኋላ፣ ወደማልመለስበት መንገድ እሄዳለሁ። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.