Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ኢዮብ 14 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም

1 “ከሴት የተወለደ ሰው፣ ዘመኑ ዐጭርና በመከራ የተሞላ ነው፤

2 እንደ አበባ ይፈካል፤ ይረግፋልም፤ እንደ ጥላ ይፈጥናል፤ አይጸናምም።

3 እንደዚህ ባለ ሰው ላይ ዐይንህን ታሳርፋለህን? ለፍርድስ በፊትህ ታቀርበዋለህን?

4 ከርኩስ ነገር ውስጥ ንጹሕን ማን ሊያወጣ ይችላል? አንድ እንኳ የሚችል የለም!

5 የሰው ዕድሜ አስቀድሞ የተወሰነ ነው፤ የወራቱንም ብዛት ወስነህ አስቀምጠሃል፤ ሊያልፈው የማይችለውንም ገደብ አኖርህለት።

6 እንግዲህ ዘመኑን እንደ ምንደኛ እስኪፈጽም ድረስ፣ ፊትህን ከርሱ መልስ፤ ተወው።

7 “ዛፍ እንኳ ቢቈረጥ፣ እንደ ገና ሊያቈጠቍጥ፣ አዳዲስ ቅርንጫፍም ሊያበቅል ተስፋ አለው።

8 ሥሩ በምድር ውስጥ ቢያረጅ፣ ጕቶው በመሬት ውስጥ ቢበሰብስም፣

9 የውሃ ሽታ ባገኘ ጊዜ ያቈጠቍጣል፤ እንደ ተተከለም ችግኝ ቅርንጫፍ ያወጣል።

10 ሰው ግን ይሞታል፤ ክንዱንም ይንተራሳል፤ ነፍሱም ትወጣለች፤ ከእንግዲህስ የት ይገኛል?

11 ውሃ ከባሕር ውስጥ እንደሚያልቅ፣ የወንዝ ውሃም ጠፍቶ እንደሚደርቅ፣

12 እንደዚሁም ሰው ይተኛል፤ ቀናም አይልም፤ ሰማይ እስከሚያልፍ ድረስ አይነቃም፤ ከእንቅልፉም አይነሣም።

13 “ምነው መቃብር ውስጥ በሰወርኸኝ! ቍጣህም እስከሚያልፍ በሸሸግኸኝ! ምነው ቀጠሮ ሰጥተህ፣ ከዚያ በኋላ ባስታወስኸኝ!

14 ሰው ከሞተ በኋላ ተመልሶ በሕይወት ይኖራል? እድሳቴ እስከሚመጣ ድረስ፣ ተጋድሎ የሞላበትን ዘመኔን ሁሉ እታገሣለሁ።

15 ትጠራኛለህ፤ እኔም እመልስልሃለሁ፤ የእጅህንም ሥራ ትናፍቃለህ።

16 በዚያ ጊዜ በርግጥ ርምጃዬን ትከታተላለህ፤ ነገር ግን ኀጢአቴን አትቈጣጠርም።

17 መተላለፌ በከረጢት ይቋጠራል፤ ኀጢአቴንም ትሸፍናለህ።

18 “ተራራ እንደሚሸረሸርና እንደሚወድቅ፣ ዐለትም ከስፍራው እንደሚወገድ፣

19 ውሃ ድንጋይን እንደሚቦረቡር፣ ጐርፍም ዐፈርን ዐጥቦ እንደሚወስድ፣ አንተም የሰውን ተስፋ ታጠፋለህ።

20 አንድ ጊዜ ፈጽመህ ትበረታለህ፤ እርሱም ያልፋል፤ ገጽታውን ትቀይራለህ፤ ትሸኘዋለህም።

21 ልጆቹ ቢከበሩ አያውቅም፤ ቢዋረዱም አያይም።

22 የገዛ አካሉ ሕመም ብቻ ይሰማዋል፤ ለራሱም ብቻ ያለቅሳል።”

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告