ኢዮብ 13 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም1 “ይህን ሁሉ ዐይኔ አይቷል፤ ጆሮዬም ሰምቶ አስተውያለሁ፤ 2 እናንተ የምታውቁትን፣ እኔም ዐውቃለሁ፤ ከእናንተ የማንስ አይደለሁም። 3 ነገር ግን ከሁሉን ቻይ አምላክ ጋራ መነጋገር እፈልጋለሁ፤ ከእግዚአብሔርም ጋራ መዋቀሥ እሻለሁ። 4 እናንተ ግን፣ በሐሰት የምትለብጡ ናችሁ፤ ሁላችሁ የማትረቡ ሐኪሞች ሆናችኋል። 5 ምነው ዝም ብትሉ! ያ ከጥበብ ይቈጠርላችሁ ነበር። 6 እንግዲህ ክርክሬን ስሙ፤ የከንፈሬንም አቤቱታ ስሙ። 7 ለእግዚአብሔር ብላችሁ በክፋት ትናገራላችሁን? ስለ እርሱስ በማታለል ታወራላችሁን? 8 ለርሱ ታደላላችሁን? ለእግዚአብሔር ጥብቅና ልትቆሙ ነውን? 9 እርሱ ቢመረምራችሁ መልካም ነገር ይገኝባችኋልን? ሰውን እንደምታታልሉ፣ ልታታልሉት ትችላላችሁን? 10 በስውር አድልዎ ብታደርጉ፣ በርግጥ እርሱ ይገሥጻችኋል። 11 ግርማው አያስደነግጣችሁምን? ክብሩስ አያስፈራችሁምን? 12 ምሳሌዎቻችሁ የዐመድ ምሳሌዎች ናቸው፣ መከላከያችሁም የጭቃ ምሽግ ነው። 13 “ዝም በሉ፤ እኔ ልናገር፤ የመጣው ይምጣብኝ። 14 ሥጋዬን በጥርሴ፣ ሕይወቴንም በእጄ ለምን እይዛለሁ? 15 ቢገድለኝም እንኳ በርሱ ተስፋ አደርጋለሁ፤ ስለ መንገዴም ፊት ለፊት እከራከረዋለሁ። 16 ኀጢአተኛ በርሱ ፊት መቅረብ ስለማይችል፣ ይህ ድፍረቴ ለመዳኔ ይሆናል። 17 ቃሌን በጥንቃቄ አድምጡ፤ እኔ የምለውንም ጆሯችሁ በሚገባ ይስማ፤ 18 እንግዲህ ጕዳዬን ይዤ ቀርቤአለሁ፤ እንደሚፈርድልኝም ዐውቃለሁ። 19 ሊከስሰኝ የሚችል አለ? ካለም፣ ዝም ብዬ ሞቴን እጠብቃለሁ። 20 “አምላክ ሆይ እነዚህን ሁለት ነገሮች ብቻ ስጠኝ፣ ያን ጊዜ ከፊትህ አልሰወርም፤ 21 እጅህን ከእኔ ላይ አንሣ፤ በግርማህም አታስፈራራኝ፤ 22 ከዚያ በኋላ ጥራኝ፤ እኔም እመልስልሃለሁ፤ ወይም እኔ ልናገር፤ አንተ መልስልኝ። 23 በደሌና ኀጢአቴ ምን ያህል ነው? መተላለፌንና ኀጢአቴን አስታውቀኝ። 24 ፊትህን ለምን ትሰውራለህ? እንደ ጠላትህስ ለምን ትቈጥረኛለህ? 25 ነፋስ ያረገፈውን ቅጠል ታስጨንቃለህን? የደረቀውንስ እብቅ ታሳድዳለህን? 26 መራራ ነገር ትጽፍብኛለህ፤ የወጣትነቴንም ኀጢአት ታወርሰኛለህ። 27 እግሬን በእግር ግንድ ታጣብቃለህ፤ ውስጥ እግሬም ላይ ምልክት አድርገህ፣ ዱካዬን አጥብቀህ ትከታተላለህ። 28 “እንደ በሰበሰ ግንድ፣ ብል እንደ በላው ልብስ፣ ሕይወት እያደር ማለቅ ነው። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.