ኢዮብ 11 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምሶፋር 1 ነዕማታዊው ሶፋር እንዲህ ሲል መለሰ፤ 2 “ይህ ሁሉ ቃል መልስ ማግኘት አይገባውምን? ወይስ ተናጋሪ ሰው እንደ እውነተኛ ይቈጠርን? 3 በውኑ የአንተ መዘላበድ ሰውን ዝም ያሰኛልን? ስታፌዝስ የሚገሥጽህ የለም? 4 አምላክንም፣ ‘ትምህርቴ የጠራ፣ በዐይንህም ፊት የጸዳሁ ነኝ’ ትለዋለህ። 5 ምነው እግዚአብሔር ቢናገርህ! ከንፈሩንም በአንተ ላይ ቢከፍት! 6 ትክክለኛ ጥበብ ባለብዙ ፈርጅ ናትና፣ የጥበብንም ምስጢር ምነው በገለጠልህ! እግዚአብሔር ለኀጢአትህ የሚገባውን እንዳላስከፈለህ ባወቅህ ነበር። 7 “የእግዚአብሔርን ጥልቅ ምስጢር ልትለካ ትችላለህን? ወይስ ሁሉን ቻዩን አምላክ መርምረህ ትደርስበታለህን? 8 ከሰማይ ይልቅ ከፍ ይላል፤ ምን ልታደርግ ትችላለህ? ከሲኦልም ይጠልቃል፤ ምን ልታውቅ ትችላለህ? 9 መጠኑ ከምድር ይልቅ ይረዝማል፤ ከባሕርም ይልቅ ይሰፋል። 10 “እርሱ ተከታትሎ መጥቶ በግዞት ቢያስቀምጥህ፣ የፍርድ ሸንጎም ቢሰበስብ፣ ማን ሊከለክለው ይችላል? 11 በእውነት እርሱ ሸፍጠኞችን ያውቃል፣ ክፋት ሲሠራም ልብ ይላል። 12 ጅል ሰው ጥበበኛ ከሚሆን ይልቅ፣ የሜዳ አህያ ሰው ሆኖ ቢወለድ ይቀላል። 13 “ነገር ግን ልብህን ብትሰጠው፣ እጅህንም ወደ እርሱ ብትዘረጋ፣ 14 በእጅህ ያለውን ኀጢአት ብታርቅ፣ ክፋትም በድንኳንህ እንዳይኖር ብታደርግ፣ 15 በዚያ ጊዜ ሳታፍር ቀና ትላለህ፤ ያለ ፍርሀት ጸንተህ ትቆማለህ፤ 16 መከራህን ትረሳለህ፤ ዐልፎ እንደ ሄደ ጐርፍም ታስበዋለህ። 17 ሕይወትህ ከቀትር ይልቅ ያበራል፤ ጨለማውም እንደ ንጋት ይሆናል። 18 ተስፋ ስላለ ተደላድለህ ትቀመጣለህ፤ ዙሪያህን ትመለከታለህ፣ ያለ ሥጋት ታርፋለህ። 19 ያለ አንዳች ሥጋት ትተኛለህ፤ ብዙ ሰዎችም ደጅ ይጠኑሃል። 20 የክፉዎች ዐይን ግን ትጨልማለች፤ ማምለጫም አያገኙም፤ ተስፋቸውም ሞት ብቻ ነው።” |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.