ኤርምያስ 48 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምስለ ሞዓብ የተነገረ መልእክት 48፥29-36 ተጓ ምብ – ኢሳ 16፥6-12 1 ስለ ሞዓብ፤ የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ናባው ትጠፋለችና ወዮላት፤ ቂርያታይም ትዋረዳለች፤ ትያዛለችም፤ ምሽጎች ይደፈራሉ፤ ይፈራርሳሉም። 2 ከእንግዲህ ሞዓብ አትከበርም፤ ሰዎች በሐሴቦን ተቀምጠው፣ ‘ኑ ያቺን አገር እናጥፋት’ ብለው ይዶልቱባታል። መድሜን ሆይ፤ አንቺም ደግሞ ጸጥ ትደረጊያለሽ፤ ሰይፍም ያሳድድሻል። 3 ከሖሮናይም የሚወጣውን ጩኸት፣ የመውደምና የታላቅ ጥፋት ድምፅ ስሙ! 4 ሞዓብ ትሰበራለች፤ ልጆቿም ጩኸት ያሰማሉ። 5 ክፉኛ እያለቀሱ፣ ወደ ሉሒት ሽቅብ ይወጣሉ፤ ስለ ደረሰባቸውም ጥፋት መራራ ጩኸት እያሰሙ፣ ወደ ሖሮናይም ቍልቍል ይወርዳሉ። 6 ሽሹ፤ ሕይወታችሁንም አትርፉ! በምድረ በዳ እንዳለ ቍጥቋጦ ሁኑ። 7 በድርጊታችሁና በብልጽግናችሁ ስለምትታመኑ፣ እናንተም ትማረካላችሁ፤ ካሞሽም ከካህናቱና ከመኳንንቱ ጋራ፣ በምርኮ ይወሰዳል። 8 በእያንዳንዱ ከተማ ላይ አጥፊ ይመጣል፤ አንድም ከተማ አያመልጥም። እግዚአብሔር ተናግሯልና፣ ሸለቆው ይጠፋል፤ ዐምባውም ይፈርሳል። 9 በርራ እንድታመልጥ፣ ለሞዓብ ክንፍ ስጧት፤ ከተሞቿም ምንም እስከማይኖርባቸው ድረስ፣ ባድማ ይሆናሉ። 10 “የእግዚአብሔርን ሥራ በቸልታ የሚያከናውን ርጉም ይሁን፤ ሰይፉን ደም ከማፍሰስ የሚከላከል የተረገመ ይሁን! 11 “ሞዓብ በአንቡላው ላይ እንዳረፈ የወይን ጠጅ፣ ከልጅነት ጀምሮ የተረጋጋ ነበረ፤ ከዕቃ ወደ ዕቃ አልተገላበጠም፤ በምርኮም አልተወሰደም፤ ቃናው እንዳለ ነው፤ መዐዛውም አልተለወጠም። 12 ስለዚህ ዕቃውን የሚገለብጡ ሰዎችን የምልክበት ጊዜ ይመጣል፤” ይላል እግዚአብሔር። “እነርሱም ይደፉታል፤ ዕቃውን ባዶ ያስቀራሉ፤ ማንቈርቈሪያዎቹንም ይሰባብራሉ። 13 የእስራኤል ቤት፤ በቤቴል ታምኖ እንዳፈረ ሁሉ፣ ሞዓብም በካሞሽ ያፍራል። 14 “እናንተ፣ ‘እኛ ተዋጊዎች ነን፤ በጦርነትም ብርቱ ነን’ ልትሉ እንዴት ቻላችሁ? 15 ሞዓብ ትጠፋለች፤ ከተሞቿም ይወረራሉ፤ ምርጥ ወጣቶቿም ወደ መታረድ ይወርዳሉ፤” ይላል ስሙ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር የሆነው ንጉሥ፤ 16 “የሞዓብ ውድቀት ተቃርቧል፤ ጥፋቱም ፈጥኖ ይመጣበታል። 17 በዙሪያው የምትኖሩ ሁሉ፤ ዝናውን የምታውቁ ሁሉ አልቅሱለት፤ ‘ብርቱው ከዘራ፣ የከበረው በትር እንዴት ሊሰበር ቻለ’ በሉ። 18 “ሞዓብን የሚያጠፋ፣ በአንቺ ላይ ይመጣልና፤ የተመሸጉ ከተሞችሽንም ያጠፋልና፤ አንቺ የዲቦን ሴት ልጅ ሆይ፤ ከክብርሽ ውረጂ፤ በደረቅም መሬት ተቀመጪ። 19 አንቺ በአሮዔር የምትኖሪ ሆይ፤ በመንገድ አጠገብ ቆመሽ ተመልከቺ፤ የሚሸሸውን ወንድ፣ የምታመልጠውንም ሴት፣ ‘ምን ተፈጠረ?’ ብለሽ ጠይቂ። 20 ሞዓብ በመፍረሱ ተዋርዷል፤ ዋይ በሉ፤ ጩኹ፤ የሞዓብን መደምሰስ፣ በአርኖን አጠገብ አስታውቁ። 21 ፍርድ በዐምባው ምድር፦ በሖሎን፣ በያሀጽና በሜፍዓት ላይ፣ 22 በዲቦን፣ በናባውና በቤትዲብላታይም ላይ፣ 23 በቂርያታይም፣ በቤትጋሙልና በቤትምዖን ላይ፣ 24 በቂርዮትና በባሶራ ላይ፤ በሩቅና በቅርብ ባሉት በሞዓብ ከተሞች ሁሉ ላይ መጥቷል። 25 የሞዓብ ቀንድ ተቈርጧል፤ እጁም ተሰባብሯል፤” ይላል እግዚአብሔር። 26 “እግዚአብሔርን ንቋልና፣ ሞዓብን በመጠጥ አስክሩት። ሞዓብ በትፋቱ ላይ ይንከባለል፤ ለመዘባበቻም ይሁን። 27 በእስራኤል ላይ ስታላግጥ አልነበረምን? ስለ እርሷ በተናገርህ ቍጥር፣ እያቃለልሃት ራስህን የምትነቀንቀውስ፣ ከሌቦች ጋራ ስትሰርቅ ተይዛለችን? 28 እናንተ በሞዓብ የምትኖሩ ሆይ፤ ከከተማ ወጥታችሁ በዐለት መካከል ኑሩ፤ በገደል አፋፍ ላይ ጐጆዋን እንደምትሠራ፣ እንደ ርግብ ሁኑ። 29 “ስለ ሞዓብ ትዕቢት፣ ስለ እብሪቱና ስለ ኵራቱ፣ ስለ ትምክሕቱና ስለ መጓደዱ፣ ስለ ልቡም ማበጥ ሰምተናል። 30 መዳፉን ዐውቃለሁ፤ ነገር ግን ከንቱ ነው፤” ይላል እግዚአብሔር። “ጕራውም ፋይዳ አይኖረውም። 31 ስለዚህ ለሞዓብ አለቅሳለሁ፤ ለሞዓብ ምድር ሁሉ ዋይ እላለሁ፤ ለቂርሔሬስ ሰዎችም የልቅሶ ድምፅ አሰማለሁ። 32 የሴባማ ወይን ሆይ፤ ለኢያዜር ካለቀስሁት እንኳ ይልቅ አለቅስልሻለሁ፤ ቅርንጫፎችሽ እስከ ባሕሩ ተዘርግተዋል፤ እስከ ኢያዜርም ደርሰዋል፤ ለመከር በደረሰው ፍሬሽና በወይንሽ ላይ፣ አጥፊው መጥቷል። 33 ከሞዓብ የአትክልት ቦታና ዕርሻ፣ ሐሤትና ደስታ ርቋል፤ የወይን ጠጅ ከመጭመቂያው እንዳይወርድ አድርቄዋለሁ፤ በእልልታ የሚጨምቀውም አይገኝም፤ በዚያ ድምፅ ቢሰማም፣ የእልልታ ድምፅ አይደለም። 34 “ከሐሴቦን እስከ ኤልያሊና እስከ ያሀጽ፣ ከዞዓር እስከ ሖሮናይም፣ እስከ ዔግላት ሺሊሺያ ድረስ፣ ጩኸታቸው ከፍ ብሎ ይሰማል፤ የኔምሬም ውሃ እንኳ ደርቋልና። 35 በመስገጃ ኰረብቶች ላይ የሚሠዉትን፣ ለአማልክታቸው የሚያጥኑትን፣ ከሞዓብ አጠፋለሁ፤” ይላል እግዚአብሔር፤ 36 “ስለዚህ ልቤ ለሞዓብ እንደ ዋሽንት ያንጐራጕራል፤ ለቂርሔሬስ ሰዎችም እንደ ዋሽንት ያንጐራጕራል። ያከማቹት ንብረት ጠፍቷልና። 37 የእያንዳንዱ ሰው ራስ፣ ጢምም ሁሉ ተላጭቷል፤ እጅ ሁሉ ተቸፍችፏል፤ ወገብም ሁሉ ማቅ ታጥቋል። 38 በሞዓብ ቤቶች ጣራ ሁሉ ላይ፣ በሕዝብም አደባባዮች፣ ሐዘን እንጂ ሌላ የለም፤ እንደማይፈለግ እንስራ፣ ሞዓብን ሰብሬአለሁና፤” ይላል እግዚአብሔር። 39 “እንዴት ተንኰታኰተ! ምንኛስ አለቀሱ! ሞዓብ እንዴት ዐፍሮ ጀርባውን አዞረ! ሞዓብ የመሰደቢያ፣ በዙሪያው ላሉትም ሁሉ የሽብር ምልክት ሆነ።” 40 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እነሆ፤ እንደ ንስር ተወርውሮ ይወርድበታል፤ ክንፎቹንም በሞዓብ ላይ ይዘረጋል። 41 ከተሞቹ ይወረራሉ፤ ምሽጎቹም ይያዛሉ፤ በዚያ ቀን የሞዓብ ጦረኞች ልብ፣ በምጥ እንደ ተያዘች ሴት ልብ ይሆናል። 42 ሞዓብ እግዚአብሔርን አቃልሏልና ይጠፋል፤ መንግሥትነቱም ይቀራል። 43 የሞዓብ ሕዝብ ሆይ፤ ሽብርና ጕድጓድ፣ ወጥመድም ይጠብቅሃል፤” ይላል እግዚአብሔር። 44 “ከሽብር የሚሸሽ ሁሉ፣ ጕድጓድ ውስጥ ይገባል፤ ከጕድጓዱም የሚወጣ፣ በወጥመድ ይያዛል፤ በሞዓብ ላይ፣ የቅጣቱን ዓመት አመጣለሁና፣” ይላል እግዚአብሔር። 45 “የሞዓብን ግንባር፣ የደንፊዎችን ዐናት የሚያቃጥል፣ እሳት ከሐሴቦን፣ ነበልባል ከሴዎን ቤት ወጥቷልና፤ ኰብላዮች በሐሴቦን ጥላ ሥር፣ ተስፋ ቈርጠው ቆመዋል። 46 ሞዓብ ሆይ፤ ወዮልህ! የካሞሽ ሕዝብ ተደምስሷል፤ ወንዶች ልጆችህ በምርኮ ተወስደዋል፤ ሴቶች ልጆችህም ተግዘዋል። 47 “ነገር ግን የኋላ ኋላ፣ የሞዓብን ምርኮ እመልሳለሁ፤” ይላል እግዚአብሔር። በሞዓብ ላይ የተወሰነው ፍርድ ይኸው ነው። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.