ኤርምያስ 47 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምስለ ፍልስጥኤማውያን የተነገረ መልእክት 1 ፈርዖን ጋዛን ድል ከማድረጉ በፊት፣ ስለ ፍልስጥኤማውያን ወደ ነቢዩ ወደ ኤርምያስ የመጣው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው፤ 2 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እነሆ፤ በሰሜን በኩል ውሃ እየሞላ ነው፤ ኀይለኛ ጐርፍ ይሆናል፤ አገሪቷንና በውስጧ ያሉትንም ሁሉ፣ ከተሞቿንና ነዋሪዎቻቸውን ያጥለቀልቃል። ሕዝቡም ድምፁን ከፍ አድርጎ ይጮኻል፤ የምድሪቱ ነዋሪ ሁሉ ዋይ ዋይ ይላል፤ 3 ከፈረስ ኮቴ ድምፅ፣ ከጠላት ሠረገላ ጩኸትና ከሠረገላው ሽክርክሪት ፍትጊያ ድምፅ የተነሣ፣ አባቶች ልጆቻቸውን ለመርዳት ወደ ኋላ መለስ አይሉም፤ እጃቸውም ስንኩል ይሆናል። 4 ፍልስጥኤማውያንን ሁሉ ለማጥፋት፣ ተርፈውም የሚረዷቸውን ሁሉ፣ ከጢሮስና ከሲዶና ለመቍረጥ፣ ቀኑ ደርሷልና። እግዚአብሔር በቀፍቶር ዳርቻ የቀሩትን፣ ፍልስጥኤማውያንን ሊያጠፋ ተነሥቷል። 5 ጋዛ በማዘን ራሷን ትላጫለች፤ አስቀሎና አፏን ትይዛለች። በሜዳማ ስፍራ የምትገኙ ቅሬታዎች ሆይ፤ እስከ መቼ ሰውነታችሁን ትቧጥጣላችሁ? 6 “ ‘ወዮ! የእግዚአብሔር ሰይፍ ሆይ፤ የማታርፈው እስከ መቼ ነው? ወደ ሰገባህ ተመልሰህ ግባ፤ ጸጥ ብለህ ተቀመጥ’ ትላላችሁ። 7 ነገር ግን እግዚአብሔር አስቀሎናንና የባሕሩን ዳርቻ፣ እንዲወጋ ሲያዝዘው፣ እንዲፈጽመውም ትእዛዝ ሲሰጠው፣ እንዴት ማረፍ ይችላል?” |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.