ኤርምያስ 43 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም1 ኤርምያስ፣ እግዚአብሔር ለእነርሱ እንዲነግራቸው የላከውን የአምላካቸውን የእግዚአብሔርን ቃል ሁሉ ለሕዝቡ ተናግሮ በጨረሰ ጊዜ፣ 2 የሆሻያ ልጅ ዓዛርያስ፣ የቃሬያ ልጅ ዮሐናንና ትዕቢተኞች የሆኑ ሰዎች ሁሉ ኤርምያስን እንዲህ አሉት፤ “ትዋሻለህ! አምላካችን እግዚአብሔር፣ ‘እዚያ ለመኖር ወደ ግብጽ አትሂዱ ብለህ ንገራቸው’ ብሎ አልላከህም፤ 3 ነገር ግን ባቢሎናውያን እንዲገድሉን ወይም ማርከው ወደ ባቢሎን እንዲወስዱን ለእነርሱ አሳልፈህ ትሰጠን ዘንድ የኔርያ ልጅ ባሮክ በእኛ ላይ አነሣሥቶሃል።” 4 ስለዚህ የቃሬያ ልጅ ዮሐናንና፣ የጦር መኰንኖቹ ሁሉ እንዲሁም ሕዝቡ በሙሉ እግዚአብሔር በይሁዳ ምድር እንዲቀመጡ ያዘዛቸውን ቃል አልሰሙም። 5 ነገር ግን፣ የቃሬያ ልጅ ዮሐናንና የጦር መኰንኖቹ ሁሉ፣ በይሁዳ ምድር ለመቀመጥ ከተበተኑበት ከአሕዛብ ሁሉ መካከል የተመለሱትን የይሁዳን ቅሬታዎች ሁሉ ይዘው ሄዱ፤ 6 በተጨማሪም ወንዶችን፣ ሴቶችንና ሕፃናትን እንዲሁም የክብር ዘበኞች አዛዥ ናቡዘረዳን በአኪቃም ልጅና በሳፋን የልጅ ልጅ በጎዶልያስ እጅ የተዋቸውን የንጉሡን ሴቶች ልጆች፣ ነቢዩ ኤርምያስንና የኔርያን ልጅ ባሮክን ወሰዷቸው፤ 7 የእግዚአብሔርንም ቃል ባለመታዘዝ ወደ ግብጽ ገቡ፤ ዘልቀውም እስከ ጣፍናስ ድረስ ሄዱ። 8 በጣፍናስም የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፤ 9 “ትልልቅ ድንጋዮች ውሰድና በጣፍናስ ባለው የፈርዖን ቤተ መንግሥት በር ላይ የይሁዳ ሰዎች እያዩ በሸክላ ጡብ ወለል ውስጥ ቅበራቸው፤ 10 እንዲህም በላቸው፤ ‘የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ አገልጋዬን የባቢሎንን ንጉሥ ናቡከደነፆርን እንዲመጣ አደርጋለሁ፤ ዙፋኑንም እዚህ በቀበርኋቸው ድንጋዮች ላይ እዘረጋለሁ፤ የንጉሥ ድንኳኑንም በላያቸው ይተክላል። 11 እርሱም መጥቶ ግብጽን ይወጋል፤ ሞት የሚገባቸውን ለሞት፣ ለምርኮ የተመደቡትን ወደ ምርኮ፣ ለሰይፍ የተዳረጉትን ለሰይፍ አሳልፎ ይሰጣል። 12 እርሱ የግብጽ አማልክት ቤተ ጣዖቶች ላይ እሳት ይለኵሳል፤ ያቃጥላቸዋልም፣ አማልክታቸውንም ማርኮ ይወስዳል። እረኛ ልብሱን እንደሚጐናጸፍ የግብጽን ምድር ተጐናጽፎ ከዚያ በሰላም ይሄዳል። 13 በግብጽ ምድር የሚገኙትን የፀሓይ አምላክ ቤተ ጣዖት ሐውልቶች ይሰባብራል፤ የግብጽንም አማልክት ቤተ ጣዖቶች በእሳት ያቃጥላል።’ ” |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.