ኤርምያስ 25 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምሰባ የምርኮ ዓመታት 1 የይሁዳ ንጉሥ የኢዮስያስ ልጅ ኢዮአቄም በነገሠ በአራተኛው ዓመት፣ ይህም ማለት በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር ዘመነ መንግሥት በመጀመሪያው ዓመት፣ ስለ ይሁዳ ሕዝብ ሁሉ ለኤርምያስ ቃል መጣለት፤ 2 ስለዚህ ነቢዩ ኤርምያስ ለይሁዳ ሕዝብ ሁሉ፣ በኢየሩሳሌም ለሚኖሩትም ሁሉ እንዲህ ሲል ተናገረ፤ 3 የይሁዳ ንጉሥ የአሞን ልጅ ኢዮስያስ ከነገሠበት ከዐሥራ ሦስተኛው ዓመት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ሃያ ሦስት ዓመት ሙሉ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ መጣ፤ ደጋግሜም ነገርኋችሁ፤ እናንተ ግን አልሰማችሁም። 4 እግዚአብሔር አገልጋዮቹን ነቢያትን ሁሉ ደጋግሞ ወደ እናንተ ላከ፤ ሆኖም አልሰማችሁም፤ ትኵረትም አልሰጣችሁትም። 5 እነርሱም እንዲህ አሉ፤ “እንግዲህ ሁላችሁ ከክፉ መንገዳችሁና ከክፉ ሥራችሁ ተመለሱ፤ እግዚአብሔር ለእናንተና ለአባቶቻችሁ በሰጣት ምድር ለዘላለም ትቀመጣላችሁ። 6 ታገለግሏቸውና ታመልኳቸው ዘንድ ሌሎቹን አማልክት አትከተሉ፤ እጃችሁ በሠራው ነገር አታስቈጡኝ፤ እኔም ክፉ አላደርግባችሁም።” 7 “ነገር ግን አልሰማችሁኝም” ይላል እግዚአብሔር፤ “እጃችሁ በሠራው ነገር አስቈጣችሁኝ፤ በራሳችሁም ላይ ክፉ ነገር አመጣችሁ።” 8 ስለዚህ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ቃሌን ስላልሰማችሁ፣ 9 የሰሜንን ሕዝብ ሁሉ፣ አገልጋዬንም የባቢሎንን ንጉሥ ናቡከደነፆርን እጠራለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “በዚህች ምድርና በነዋሪዎቿም ላይ፣ በአካባቢዋም ባሉ ሕዝቦች ሁሉ ላይ አመጣባቸዋለሁ፤ ፈጽሜም አጠፋቸዋለሁ፤ ሰዎች የሚጸየፏቸውና የሚሣለቁባቸው፣ የዘላለምም ባድማ አደርጋቸዋለሁ፤ 10 የደስታንና የእልልታን ድምፅ፣ የሙሽራውንና የሙሽራዪቱን ድምፅ፣ የወፍጮን ድምፅና የመብራትን ብርሃን አስቀራለሁ። 11 አገሪቱ በሞላ ባድማና ጠፍ ትሆናለች፤ እነዚህም ሕዝቦች ለባቢሎን ንጉሥ ሰባ ዓመት ይገዛሉ። 12 “ነገር ግን ሰባው ዓመት ከተፈጸመ በኋላ፣ የባቢሎንን ንጉሥና ሕዝቡን፣ የባቢሎናውያንንም ምድር ስለ በደላቸው እቀጣቸዋለሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “ለዘላለምም ባድማ አደርጋታለሁ፤ 13 በምድሪቱ ላይ የተናገርሁትን ሁሉ ይኸውም በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውንና ኤርምያስ በሕዝቦች ሁሉ ላይ የተናገረውን ትንቢት አመጣባታለሁ። 14 ሕዝቧም ለብዙ ሕዝቦችና ለታላላቅ ነገሥታት ባሮች ይሆናሉ፤ እንደ አድራጎታቸውና እንደ እጃቸውም ሥራ እከፍላቸዋለሁ።” የቍጣው ጽዋ 15 የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፤ “በቍጣዬ የወይን ጠጅ የተሞላውን ይህን ጽዋ ከእጄ ውሰድ፤ እኔ ወደምልክህም ሕዝቦች ሁሉ ሄደህ አጠጣቸው። 16 በጠጡም ጊዜ ይንገዳገዳሉ፤ በመካከላቸው ከምሰድደው ሰይፍ የተነሣ ያብዳሉ።” 17 ስለዚህ ጽዋውን ከእግዚአብሔር እጅ ተቀብዬ እርሱ ወደ ላከኝ ሕዝቦች ሁሉ ሄድሁ፤ እንዲጠጡትም አደረግሁ፦ 18 ዛሬ እንደ ሆነው ሁሉ ባድማና ሰዎች የሚጸየፏቸው መዘባበቻና ርግማን እንዲሆኑ፣ ኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ከተሞች፣ ነገሥታቷንና ባለሥልጣኖቿን፣ 19 የግብጽን ንጉሥ ፈርዖንን፣ አገልጋዮቹን፣ ባለሥልጣኖቹንና ሕዝቡን ሁሉ፣ 20 በዚያ የሚኖሩትን ድብልቅ ሕዝብ ሁሉ፣ የዖፅ ምድር ነገሥታትን ሁሉ፣ በአስቀሎና፣ በጋዛ፣ በአቃሮንና በአዛጦንም ሕዝብ ቅሬታ ያሉትን የፍልስጥኤም ነገሥታት፣ 21 ኤዶምን፣ ሞዓብን፣ አሞንን፣ 22 የጢሮስንና የሲዶናን ነገሥታት ሁሉ፣ ከባሕሩ ማዶ ያሉ የጠረፍ ምድር ነገሥታትን፣ 23 ድዳንን፣ ቴማንን፣ ቡዝን፣ ጠጕራቸውን ዙሪያውን የሚከረከሙትን ሕዝብ ሁሉ፣ 24 የዐረብ ነገሥታትን ሁሉ፣ በምድረ በዳ የሚኖሩትን የድብልቅ ሕዝብ ነገሥታት ሁሉ፣ 25 የዘምሪ፣ የኤላምና የሜዶን ነገሥታትን ሁሉ፣ 26 በቅርብና በሩቅ ያሉትን የሰሜን ነገሥታትንም ሁሉ በማከታተል፣ በምድር ላይ ያሉትን መንግሥታት ሁሉ አጠጣኋቸው፤ ከእነዚህም ሁሉ በኋላ የሼሻክ ንጉሥ ደግሞ ይጠጣል። 27 “አንተም እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ጠጡ፤ ስከሩ፤ አስታውኩም፤ ዳግመኛም ላትነሡ በመካከላችሁ በምሰድደው ሰይፍ ፊት ውደቁ።” 28 ነገር ግን ጽዋውን ከእጅህ ለመውሰድና ለመጠጣት እንቢ ካሉ፣ እንዲህ በላቸው፤ “የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በግድ ትጠጣላችሁ። 29 እነሆ፤ ስሜ የተጠራበትን ከተማ ማጥፋት እጀምራለሁ፤ ታዲያ ያለ ቅጣት ታመልጣላችሁን? ሳትቀጡ አትለቀቁም፤ በምድር በሚኖሩት ሁሉ ላይ ሰይፍን እጠራለሁና ሳትቀጡ አታመልጡም፤” ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።’ 30 “እንግዲህ ይህን ቃል ሁሉ ትንቢት ተናገርባቸው፤ እንዲህም በላቸው፣ “ ‘እግዚአብሔር ከላይ ይጮኻል፤ ከቅዱስ ማደሪያው ነጐድጓዳማ ድምፁን ያሰማል፤ በራሱ ምድር ላይ እጅግ ይጮኻል፤ እንደ ወይን ጨማቂዎች፣ በምድር በሚኖሩት ሁሉ ላይም ያስገመግማል፤ 31 እግዚአብሔር ከሕዝቦች ጋራ ይፋረዳልና፣ ታላቅ ጩኸት እስከ ምድር ዳርቻ ያስተጋባል፤ በሰው ሁሉ ላይ ፍርድን ያመጣል፤ ክፉዎችንም ለሰይፍ ይዳርጋል’ ” ይላል እግዚአብሔር። 32 የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እነሆ፤ ጥፋት፣ ከአገር ወደ አገር እየተዛመተ መጥቷል፤ ብርቱ ዐውሎ ነፋስ፣ ከምድር ዳርቻ ተነሥቷል።” 33 በዚያ ጊዜ በእግዚአብሔር የተገደሉት ከምድር ዳር እስከ ምድር ዳር በሁሉ ስፍራ ተረፍርፈው ይታያሉ፤ እንደ ጕድፍ በምድር ላይ ይጣላሉ እንጂ፣ አይለቀስላቸውም፤ ሬሳቸውም አይሰበሰብም፤ አይቀበርምም። 34 እናንተ እረኞች፤ አልቅሱ፤ ዋይ በሉ፤ እናንተ የመንጋው ጌቶች፤ በዐመድ ላይ ተንከባለሉ፤ የምትታረዱበት ቀን ደርሷልና፤ እንደ ውብ የሸክላ ዕቃ ወድቃችሁ ትከሰከሳላችሁ። 35 እረኞች የሚሸሹበት፣ የመንጋ ጠባቂዎችም የሚያመልጡበት የለም። 36 እግዚአብሔር ማሰማሪያቸውን አጥፍቷልና፣ የእረኞችን ጩኸት፣ የመንጋ ጠባቂዎችን ዋይታ ስሙ። 37 ከእግዚአብሔር ጽኑ ቍጣ የተነሣ፣ ሰላማዊው ምድር ባድማ ይሆናል። 38 እንደ አንበሳ ከጐሬው ይወጣል፤ ከአስጨናቂው ሰይፍ፣ ከቍጣውም የተነሣ፣ ምድራቸው ባድማ ትሆናለች። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.