ኤርምያስ 19 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም1 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ሄደህ፣ ከሸክላ ሠሪ ገንቦ ግዛ፤ ከሕዝቡና ከካህናቱ መካከል ሽማግሌዎች የሆኑትን አንዳንዶቹን ይዘህ፣ 2 በገል በር መግቢያ አጠገብ ወዳለው ወደ ሄኖም ልጅ ሸለቆ ውጣ። በዚያም የምነግርህን ቃል ተናገር፤ 3 እንዲህም በል፤ ‘የይሁዳ ነገሥታትና በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሆይ፤ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ለሰሚው ሁሉ ጆሮ የሚዘገንን ክፉ ነገር እነሆ በዚህ ስፍራ አመጣለሁ፤ 4 እኔን ትተውኝ፣ ይህን ስፍራ የባዕድ አማልክት ቦታ አድርገውታልና። እነርሱም ሆኑ አባቶቻቸው፣ የይሁዳ ነገሥታትም ለማያውቋቸው አማልክት ሠውተዋል፤ ይህንም ስፍራ በንጹሓን ደም ሞልተውታል፤ 5 እኔም ያላዘዝኋቸውን፣ ያልተናገርኋቸውን፣ ፈጽሞም ያላሰብሁትን፣ ወንዶች ልጆቻቸውን በእሳት ሊሠዉለት ለበኣል መስገጃ ኰረብቶች ሠርተዋል። 6 ስለዚህ ሰዎች ይህን ስፍራ የዕርድ ሸለቆ እንጂ ከእንግዲህ ቶፌት ወይም የሄኖም ልጅ ሸለቆ ብለው የማይጠሩበት ዘመን ይመጣል፤” ይላል እግዚአብሔር። 7 “ ‘በዚህ ስፍራ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ዕቅድ አፈርሳለሁ፤ በጠላቶቻቸው ፊት ሕይወታቸውን በሚሹት እጅ በሰይፍ እንዲወድቁ አደርጋለሁ፤ ሬሳቸውንም ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት ምግብ አድርጌ እሰጣለሁ። 8 ይህችን ከተማ ድምጥማጧን አጠፋለሁ፤ የድንጋጤና መሣለቂያም ምልክት አደርጋታለሁ፤ በዚያም የሚያልፉ ሁሉ ከቍስሎቿም የተነሣ ወይ ጉድ! ይላሉ፣ ያሾፋሉም። 9 የወንዶችና የሴቶች ልጆቻቸውን ሥጋ እንዲበሉ አደርጋለሁ፤ ሕይወታቸውን ለማጥፋት የሚሹ ጠላቶቻቸው ከብበው ሲያስጨንቋቸው፣ አንዱ የሌላውን ሥጋ ይበላል።’ 10 “ገንቦውንም ከአንተ ጋራ በሄዱ ሰዎች ፊት ትሰብራለህ፤ 11 እንዲህም ትላቸዋለህ፤ ‘የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “የሸክላ ሠሪው ገንቦ እንደ ተሰበረና ሊጠገን እንደማይቻል፣ ይህን ሕዝብና ይህችን ከተማ እንዲሁ እሰብራለሁ፤ የቀብር ቦታ ከመታጣቱ የተነሣ ሙታናቸውን በቶፌት ይቀብራሉ። 12 በዚህ ስፍራና በውስጡም በሚኖሩት ላይ ይህን አደርጋለሁ” ይላል እግዚአብሔር። ይህችን ከተማ እንደ ቶፌት አደርጋታለሁ። 13 በጣራዎቻቸው ላይ ለሰማይ ሰራዊት ዕጣን የታጠነባቸውና ለባዕዳን አማልክት የመጠጥ ቍርባን የቀረበባቸው፣ የኢየሩሳሌም ቤቶችና የይሁዳ ነገሥታት ቤቶች እንደ ቶፌት የረከሱ ይሆናሉ።’ ” 14 ኤርምያስም እግዚአብሔር ትንቢት እንዲናገር ልኮት ከነበረበት ከቶፌት ተመልሶ፣ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አደባባይ በመቆም፣ ለሕዝቡ ሁሉ እንዲህ አለ፤ 15 “የእስራኤል አምላክ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እነሆ ዐንገታቸውን በማደንደን ቃሌን ስላልሰሙ በዚህች ከተማና በዙሪያዋ ባሉ መንደሮች ሁሉ ላይ ላደርስ ያሰብሁትን ጥፋት ሁሉ አመጣለሁ።’ ” |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.