ኤርምያስ 14 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምድርቅ፣ ራብ፣ ሰይፍ 1 ስለ ድርቅ ወደ ኤርምያስ የመጣው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው፤ 2 “ይሁዳ ታለቅሳለች፤ ከተሞቿም ይማቅቃሉ፤ በምድር ላይ ተቀምጠው ይቈዝማሉ፤ ጩኸትም ከኢየሩሳሌም ወጥቶ ይሰማል። 3 መሳፍንት አገልጋዮቻቸውን ውሃ ፍለጋ ይሰዳሉ፤ እነርሱ ወደ ውሃ ጕድጓዶች ይወርዳሉ፤ ነገር ግን ውሃ አያገኙም፤ ዐፍረውና ተስፋ ቈርጠው፣ ራሳቸውን ተከናንበው፣ ባዶ እንስራ ይዘው ይመለሳሉ። 4 በምድሪቱ ዝናብ ስለሌለ፣ መሬቱ ተሰነጣጥቋል፤ ገበሬዎችም ዐፍረው፣ ራሳቸውን ተከናንበዋል። 5 አንዳች ሣር ባለመኖሩ፣ የሜዳ አጋዘን እንኳ፣ እንደ ወለደች ግልገሏን ጥላ ትሄዳለች። 6 የሜዳ አህዮች ባድማ ኰረብቶች ላይ ቆሙ፤ እንደ ቀበሮም አየር ፍለጋ አለከለኩ፤ ግጦሽ ባለመገኘቱ፣ ዐይኖቻቸው ፈዘዙ።” 7 እግዚአብሔር ሆይ፤ ከአንተ መኰብለል አብዝተናል፤ በአንተም ላይ ዐምፀናል፤ ኀጢአታችን ቢመሰክርብንም እንኳ፣ ስለ ስምህ ብለህ አንድ ነገር አድርግልን። 8 አንተ የእስራኤል ተስፋ፤ በጭንቀት ጊዜ አዳኙ፣ ለምን በምድሪቱ እንደ ባዕድ፣ እንደ ሌት ዐዳሪ መንገደኛ ትሆናለህ? 9 ግራ እንደ ተጋባ ሰው፣ ለመታደግም ኀይል እንዳጣ ተዋጊ ትሆናለህ? እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ በመካከላችን አለህ፤ በስምህም ተጠርተናል፤ እባክህ አትተወን። 10 እግዚአብሔር ስለዚህ ሕዝብ እንዲህ ይላል፤ “መቅበዝበዝ እጅግ ይወድዳሉ፤ እግሮቻቸው አይገቱም፤ ስለዚህ እግዚአብሔር በእነርሱ ደስ አይለውም፤ አሁን በደላቸውን ያስባል፤ በኀጢአታቸውም ይቀጣቸዋል።” 11 እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፤ “ለዚህ ሕዝብ በጎነት አትጸልይ፤ 12 ቢጾሙም ጩኸታቸውን አልሰማም፤ የሚቃጠል መሥዋዕትና የእህል ቍርባን ቢያቀርቡም አልቀበላቸውም፤ ነገር ግን በሰይፍ፣ በራብና በቸነፈር አጠፋቸዋለሁ።” 13 እኔም፣ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ወዮ! ነቢያቱ ‘ሰይፍ አታዩም፤ ራብም አያገኛችሁም፤ ነገር ግን በዚህ ስፍራ ዘለቄታ ያለው እውነተኛ ሰላም እሰጣችኋለሁ’ ይላል ይሏቸዋል” አልሁ። 14 እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፤ “ነቢያቱ በስሜ የሐሰት ትንቢት ይናገራሉ፤ እኔ አልላክኋቸውም፤ አላዘዝኋቸውም፤ አልተናገርኋቸውምም። የሐሰት ራእይ፣ ሟርት፣ ከንቱ ነገርንና የልባቸውን ሽንገላ ይተነብዩላችኋል። 15 ስለዚህ በስሜ የሐሰት ትንቢት ስለሚናገሩ ነቢያት እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ እኔ ሳልልካቸው፣ ‘ሰይፍና ራብ በዚች ምድር ላይ አይመጣም’ የሚሉ እነዚህ ነቢያት በሰይፍና በራብ ይጠፋሉ፤ 16 ትንቢቱ የተነገረለትም ሕዝብ ከሰይፍና ከራብ የተነሣ በኢየሩሳሌም አደባባዮች ይወድቃል፤ እነርሱንም ሆነ ሚስቶቻቸውን ወይም ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን የሚቀብራቸው አይገኝም። ለበደላቸው የሚገባውንም ቅጣት በላያቸው አወርዳለሁ። 17 “ይህን ቃል እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ “ ‘ድንግሊቱ ልጄ፣ ሕዝቤ፣ በታላቅ ስብራት፣ በብርቱ ቍስል ተመትታለችና ዐይኖቼ ቀንና ሌሊት፣ ሳያቋርጡ እንባ ያፈስሳሉ 18 ወደ ገጠር ብወጣ፣ በሰይፍ የተገደሉትን አያለሁ፤ ወደ ከተማ ብገባ፣ በራብ የወደቁትን አያለሁ ነቢዩም ካህኑም፣ ወደማያውቁት አገር ሸሽተዋል።’ ” 19 ይሁዳን ፈጽመህ ጥለኸዋልን? ነፍስህስ ጽዮንን ተጸየፈቻትን? ፈውስ እስከማይገኝልን ድረስ፣ ለምን ክፉኛ መታኸን? ሰላምን ተስፋ አደረግን፤ ሆኖም በጎ ነገር አላገኘንም፤ የፈውስን ጊዜ ተጠባበቅን፤ ነገር ግን ሽብር ብቻ ሆነ። 20 እግዚአብሔር ሆይ፤ ክፋታችንን ዐውቀናልና፤ የአባቶቻችንን በደል ተረድተናልና፤ በርግጥም በአንተ ላይ ኀጢአት ሠርተናል። 21 ስለ ስምህ ብለህ አትናቀን፤ የክብርህንም ዙፋን አታዋርድ። ከእኛ ጋራ የገባኸውን ኪዳን ዐስብ፤ አታፍርሰውም። 22 ከአሕዛብ ከንቱ ጣዖቶች መካከል ዝናብ ሊያዘንብ የሚችል አለን? ሰማያትስ በራሳቸው ማካፋት ይችላሉን? አይ! አይችሉም፣ እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ፤ ይህን ሁሉ የምታደርግ አንተ ነህ፣ ስለዚህም ተስፋችን በአንተ ላይ ነው። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.