Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ኤርምያስ 11 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


ያልተከበረው ኪዳን

1 ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው፤

2 “የዚህን ኪዳን ቃል ስማ፤ ለይሁዳ ሕዝብና በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ ሰዎች ንገራቸው፤

3 የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል በላቸው፤ ‘ለዚህ ኪዳን ቃል የማይታዘዝ ሰው የተረገመ ይሁን፤

4 ይህም ትእዛዝ የቀድሞ አባቶቻችሁን ከግብጽ ምድር፣ ከብረት ማቅለጫው ምድጃ ባወጣኋቸው ጊዜ ድምፄን ቢሰሙ፣ ትእዛዜንም ሁሉ ቢጠብቁ፣ እነርሱ ሕዝቤ፣ እኔም አምላካቸው እንድሆን የሰጠኋቸው ቃል ነው፤

5 ዛሬም እንደ ሆነው ሁሉ ወተትና ማር የምታፈስሰውን ምድር ለአባቶቻችሁ ለመስጠት የገባሁትን መሐላ እፈጽማለሁ።’ ” እኔም፣ “እግዚአብሔር ሆይ፤ አሜን” ብዬ መለስሁ።

6 እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፤ “ይህን ቃል ሁሉ በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም አደባባዮች ተናገር፤ እንዲህም በል፤ ‘የዚህን ኪዳን ቃል ስሙ፤ አድርጉትም።

7 የቀድሞ አባቶቻችሁን ከግብጽ ምድር ካወጣሁበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ፣ “ታዘዙኝ” በማለት ደጋግሜ አስጠነቀቅኋቸው።

8 እነርሱ ግን የክፉ ልባቸውን እልኸኝነት ተከተሉ እንጂ አልታዘዙኝም፤ ጆሯቸውንም ወደ እኔ አላዘነበሉም፤ ስለዚህ እንዲከተሉት አዝዤአቸው ያላደረጉትን የዚህን ኪዳን ርግማን ሁሉ አመጣሁባቸው።’ ”

9 እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፤ “በይሁዳ ሕዝብና በኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ዘንድ ዐድማ ተገኝቷል።

10 ቃሌን መስማት ወዳልፈለጉት ወደ ቀድሞ አባቶቻቸው ኀጢአት ተመለሱ፤ ሊያገለግሏቸውም ሌሎችን አማልክት ተከተሉ። የእስራኤልና የይሁዳ ቤት ከቀድሞ አባቶቻቸው ጋራ የገባሁትን ኪዳን አፈረሱ።

11 ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ሊያመልጡት የማይችሉትን ጥፋት አመጣባቸዋለሁ፤ ወደ እኔ ቢጮኹም አልሰማቸውም።

12 የይሁዳ ከተሞችና የኢየሩሳሌም ሕዝቦች ወደሚያጥኑላቸው አማልክት ሄደው ይጮኻሉ፤ እነርሱ ግን በመከራቸው ጊዜ ከቶ ሊረዷቸው አይችሉም።

13 ይሁዳ ሆይ፤ የአማልክትህ ቍጥር የከተሞችህን ብዛት ያህል ነው፤ አሳፋሪ ለሆነው ጣዖት፣ ለበኣል ማጠኛ የሠራችኋቸው መሠዊያዎቻችሁ ብዛት የኢየሩሳሌምን መንገዶች ያህል ነው።’

14 “በተጨነቁ ጊዜ ወደ እኔ ሲጮኹ አልሰማቸውምና አንተም ስለዚህ ሕዝብ አትጸልይ፤ ልመና አታቅርብ፤ አትማጠን።

15 “ወዳጄ፣ ከብዙዎች ጋራ ተንኰሏን እየሸረበች፣ በቤቴ ውስጥ ምን ጕዳይ አላት? ስእለት ወይም የመሥዋዕት ሥጋ ቅጣትሽን ሊያስቀርልሽ ይችላልን? እነዚህንስ በመፈጸም፣ ደስተኛ መሆን ትችያለሽን?”

16 እግዚአብሔር፣ የተዋበ ፍሬ ያላት፣ የለመለመች የወይራ ዛፍ ብሎሽ ነበር፤ አሁን ግን በታላቅ ዐውሎ ነፋስ ድምፅ፣ እሳት ያነድድባታል፤ ቅርንጫፎቿ ይሰባበራሉ።

17 የእስራኤልና የይሁዳ ቤት ለበኣል በማጠን ባደረጉት ክፋት ስላስቈጡኝ፣ አንቺን የተከለሽ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ክፉ ነገር ዐውጆብሻል።


በኤርምያስ ላይ የተደረገ ሤራ

18 እግዚአብሔር ስውር ዕቅዳቸውን ገለጠልኝ፤ እኔም ዐወቅሁ፤ በዚያ ጊዜ ሥራቸውን አሳይቶኝ ነበርና።

19 እኔም ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት ነበርሁ፤ እነርሱም፣ “ዛፉን ከፍሬው ጋራ እንቍረጥ፤ ከሕያዋን ምድር እናጥፋው፤ ከእንግዲህም ወዲያ ስሙ አይታሰብ” ብለው እንዳደሙብኝ ዐላወቅሁም ነበር።

20 ልብንና ኵላሊትን የምትመረምር፣ በጽድቅም የምትፈርድ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ ጕዳዬን ላንተ ትቻለሁና፤ በእነርሱ ላይ የምትፈጽመውን በቀል ልይ።

21 “እንግዲህ ሕይወትህን ለማጥፋት ለሚሹና፣ ‘በእግዚአብሔር ስም ትንቢት አትናገር፤ አለዚያ በእጃችን ትሞታለህ’ ለሚሉህ ለዓናቶት ሰዎች እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤

22 ስለዚህ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እነሆ እኔ እቀጣቸዋለሁ፤ ጕልማሶቻቸው በሰይፍ፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውም በራብ ይሞታሉ።

23 በሚቀጡበት ዓመት በዓናቶት ሰዎች ላይ መዓት ስለማመጣ፣ ከእነርሱ የሚተርፍ አንድም አይኖርም።’ ”

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告