ኢሳይያስ 7 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምየዐማኑኤል ምልክትነት 1 የዖዝያን የልጅ ልጅ፣ የኢዮአታም ልጅ አካዝ የይሁዳ ንጉሥ በነበረበት ዘመን፣ የሶርያ ንጉሥ ረአሶንና የእስራኤል ንጉሥ የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ ኢየሩሳሌምን ሊወጉ ወጡ፤ ነገር ግን ድል ሊያደርጓት አልቻሉም። 2 ለዳዊት ቤት፣ “ሶርያና ኤፍሬም ተባብረዋል” የሚል ወሬ በደረሰ ጊዜ፣ የዱር ዛፍ በነፋስ እንደሚናወጥ የአካዝና የሕዝቡ ልብ እንዲሁ ተናወጠ። 3 እግዚአብሔርም ኢሳይያስን እንዲህ አለው፤ “አንተና ልጅህ ሸአር ያሹብ አካዝን ለመገናኘት ወደ ልብስ ዐጣቢው ዕርሻ በሚወስደው መንገድ ወዳለው ወደ ላይኛው የኵሬ መስኖ ጫፍ ውጡ፤ 4 እንዲህም በለው፤ ‘ተጠንቀቅ፤ ተረጋጋ፤ አትፍራ፤ በእነዚህ ከእሳት ተርፈው በሚጤሱት በሁለቱ የዕንጨት ጕማጆች፣ በሶርያና በንጉሥዋ በረአሶን እንዲሁም በሮሜልዩ ልጅ ቍጣ አትሸበር። 5 ሶርያ ኤፍሬምና፣ የሮሜልዩ ልጅ ሊያጠፉህ እንዲህ ብለው ተማከሩ፤ 6 “ይሁዳን እንውረር፤ እንበታትነው፤ ተከፋፍለንም እንግዛው፤ የጣብኤልንም ልጅ እናንግሥባት።” 7 ጌታ እግዚአብሔር ግን እንዲህ ይላል፤ “ ‘ይህ ምክራቸው አይፈጸምም፤ ከቶም አይደረግም፤ 8 የሶርያ ራስ ደማስቆ፣ የደማስቆ ራስ ረአሶን ነውና፤ በስድሳ ዐምስት ዓመት ውስጥ፣ የኤፍሬም ሕዝብ ይበታተናል፤ ሕዝብ መሆኑም ይቀራል። 9 የኤፍሬም ራስ ሰማርያ፣ የሰማርያም ራስ የሮሜልዩ ልጅ ነው። እንግዲህ በእምነታችሁ ካልጸናችሁ፣ ፈጽሞ መቆም አትችሉም።’ ” 10 እንደ ገናም እግዚአብሔር አካዝን እንዲህ አለው፤ 11 “ከጥልቁ ጥልቅ ወይም ከከፍታው ከፍታ ምልክት እንዲሰጥህ ከእግዚአብሔር ከአምላክህ ለምን።” 12 አካዝ ግን፣ “አልለምንም፣ እግዚአብሔርንም አልፈታተንም” አለ። 13 ኢሳይያስም እንዲህ አለ፤ “እናንተ የዳዊት ቤት ሆይ፤ ስሙ! የሰውን ትዕግሥት መፈታተናችሁ አንሶ የአምላኬን ትዕግሥት ትፈታተናላችሁን? 14 ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤ እነሆ፤ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፤ ስሙንም ዐማኑኤል ትለዋለች። 15 ክፉውን መተውና መልካሙን መምረጥ ሲችል ቅቤና ማር ይበላል። 16 ነገር ግን ሕፃኑ ክፉውን መተውና መልካሙን መምረጥ ከመቻሉ በፊት የፈራሃቸው የሁለቱ ነገሥታት ምድር ባድማ ይሆናል። 17 ኤፍሬም ከይሁዳ ከተለየበት ቀን ጀምሮ እግዚአብሔር ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ዘመን በአንተ፣ በሕዝብህና በአባትህ ቤት ላይ ያመጣል፤ የሚያመጣውም የአሦርን ንጉሥ ነው።” 18 በዚያ ቀን እግዚአብሔር ራቅ ካሉት ከግብጽ ወንዞች ዝንቦችን፣ ከአሦርም ምድር ንቦችን በፉጨት ይጠራል። 19 እነርሱም በሙሉ መጥተው፣ በየበረሓው ሸለቆ፣ በየዐለቱ ንቃቃት፣ በየእሾኹ ቍጥቋጦና በየውሃው ጕድጓድ ሁሉ ይሰፍራሉ። 20 በዚያ ቀን፣ እግዚአብሔር ከኤፍራጥስ ወንዝ ማዶ በተከራየው ምላጭ፣ ማለትም በአሦር ንጉሥ፣ የራስና የእግር ጠጕራችሁን እንዲሁም ጢማችሁን ይላጫል። 21 በዚያ ቀን፣ አንድ ሰው አንዲት ጊደርና ሁለት በግ ብቻ ይተርፈዋል። 22 ከሚሰጡትም የተትረፈረፈ ወተት ቅቤ ይበላል፤ በምድሪቱም የቀሩ ሁሉ ቅቤና ማር ይበላሉ። 23 በዚያ ቀን ሺሕ ሰቅል ብር የሚያወጣ አንድ ሺሕ የወይን ተክል የነበረበት ቦታ ሁሉ፣ ኵርንችትና እሾኽ ብቻ ይሆናል። 24 ምድሪቱ በኵርንችትና በእሾኽ ስለምትሸፈን፣ ሰዎች ወደዚያ የሚገቡት ቀስትና ፍላጻ ይዘው ነው፤ 25 ኵርንችትና እሾኹን በመፍራት ከዚህ በፊት በመቈፈሪያ ተቈፍረው ወደ ነበሩት ወደ እነዚያ ኰረብቶች ሁሉ ከእንግዲህ አትሄድም፤ ነገር ግን የከብቶች መሰማሪያና የበጎች መፈንጫ ቦታ ይሆናሉ። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.