Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ኢሳይያስ 66 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


ፍርድና ተስፋ

1 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ሰማይ ዙፋኔ ነው፤ ምድርም የእግሬ ማሳረፊያ ናት፤ ታዲያ ቤት የት ትሠሩልኛላችሁ? ይላል ጌታ፤ ወይስ ማረፊያ የሚሆነኝ ቦታ የት ነው?

2 እነዚህን ነገሮች ሁሉ እጄ አልሠራችምን? እንዲገኙስ ያደረግሁ እኔ አይደለሁምን?” ይላል እግዚአብሔር። “ነገር ግን እኔ ወደዚህ፣ ትሑት ወደ ሆነና መንፈሱ ወደ ተሰበረ፣ በቃሌም ወደሚንቀጠቀጥ ሰው እመለከታለሁ።

3 ነገር ግን ወይፈን የሚሠዋልኝ፣ ሰው እንደሚገድል ነው፤ የበግ ጠቦት የሚያቀርብልኝ፣ የውሻ ዐንገት እንደሚሰብር ሰው ነው፤ የእህል ቍርባን የሚያዘጋጅልኝ፣ የዕሪያ ደም እንደሚያቀርብልኝ ሰው ነው፤ የመታሰቢያን ዕጣን የሚያጥንልኝም፣ ጣዖትን እንደሚያመልክ ሰው ነው፤ የገዛ መንገዳቸውን መርጠዋል፤ ነፍሳቸውም በርኩሰታቸው ደስ ይላታል።

4 ስለዚህ ችግር እንዲደርስባቸው አደርጋለሁ፤ የፈሩትንም አመጣባቸዋለሁ፤ በተጣራሁ ጊዜ የመለሰ፣ በተናገርሁ ጊዜ ያደመጠ ሰው የለምና። በፊቴ ክፉ ነገር አደረጉ፤ የሚያስከፋኝንም መረጡ።”

5 እናንተ በቃሉ የምትንቀጠቀጡ፣ ይህን የእግዚአብሔር ቃል ስሙ፤ “እናንተ ወንድሞቻችሁ የጠሏችሁ፣ ስለ ስሜም አውጥተው የጣሏችሁ፣ ‘እስኪ እግዚአብሔር ይክበርና፣ የእናንተን ደስታ እንይ!’ አሏችሁ፤ ይሁን እንጂ ማፈራቸው አይቀርም።

6 ያን የጩኸት ድምፅ ከከተማው ስሙ! ያን ጫጫታ ከቤተ መቅደሱ ስሙ! ይኸውም የእግዚአብሔር ድምፅ ነው፤ ለጠላቶቹም የሚገባቸውን ሁሉ ይከፍላቸዋል።

7 “ከማማጧ በፊት፣ ትወልዳለች፤ በምጥ ጣር ከመያዟ በፊት፣ ወንድ ልጅ ትገላገላለች።

8 እንዲህ ያለ ነገር ማን ሰምቶ ያውቃል? እንዲህ ያለ ነገርስ ማን አይቶ ያውቃል? አገር በአንድ ጀንበር ይፈጠራልን? ወይስ ሕዝብ በቅጽበት ይገኛል? ጽዮንን ምጥ ገና ሲጀምራት፣ ልጆቿን ወዲያውኑ ትወልዳለች።

9 ሊወለድ የተቃረበውን፣ እንዳይወለድ አደርጋለሁን?” ይላል እግዚአብሔር። “በሚገላገሉበት ጊዜስ፣ ማሕፀን እዘጋለሁን?” ይላል አምላክሽ።

10 “ወዳጆቿ የሆናችሁ ሁሉ፣ ከኢየሩሳሌም ጋራ ደስ ይበላችሁ፤ ስለ እርሷም ሐሤት አድርጉ፤ ለርሷ ያለቀሳችሁ ሁሉ፣ ከርሷ ጋራ እጅግ ደስ ይበላችሁ።

11 ከሚያጽናኑ ጡቶቿ፣ ትጠባላችሁ፤ ትረካላችሁም፤ እስክትረኩም ትጠጣላችሁ፤ በተትረፈረፈ ሀብቷም ትደሰታላችሁ።”

12 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እነሆ፤ ሰላምን እንደ ወንዝ ውሃ አፈስስላታለሁ፤ የመንግሥታትንም ብልጽግና እንደ ጅረት ውሃ አጐርፍላታለሁ፤ ትጠባላችሁ፤ በዕቅፏም ትያዛላችሁ፤ በጭኖቿም ላይ ትፈነድቃላችሁ።

13 እናት ልጇን እሹሩሩ እንደምትል፣ እኔም እናንተን እሹሩሩ እላችኋለሁ፤ በኢየሩሳሌምም ትጽናናላችሁ።”

14 ይህን ስታዩ፣ ልባችሁ ሐሤት ያደርጋል፤ ዐጥንቶቻችሁም እንደ ሣር ይለመልማሉ፤ የእግዚአብሔር እጅ ከባሮቹ ጋራ መሆኑ ይታወቃል፤ ቍጣው ግን በጠላቶቹ ላይ ይገለጣል።

15 እነሆ፤ እግዚአብሔር በእሳት ነበልባል ይመጣል፤ ሠረገሎቹም እንደ ዐውሎ ነፋስ ናቸው፤ ንዴቱን በቍጣ፣ ተግሣጹንም በእሳት ነበልባል ይገልጣል።

16 በእሳትና በሰይፍ፣ እግዚአብሔር ፍርዱን በሰው ሁሉ ላይ ያመጣል፤ በእግዚአብሔር ሰይፍ የሚታረዱት ብዙ ይሆናሉ።

17 “ወደ አትክልት ቦታዎች ለመሄድና ከተክሎቹ አንዱን ለማምለክ ራሳቸውን የሚቀድሱና የሚያነጹ፣ የዕሪያዎችንና የዐይጦችን ሥጋ፣ የረከሱ ነገሮችንም የሚበሉ ሁሉ የመጨረሻ ፍርዳቸውን በአንድነት ይቀበላሉ” ይላል እግዚአብሔር።

18 “እኔም ሥራቸውንና ሐሳባቸውን ስለማውቅ፣ መንግሥታትንና ልሳናትን ሁሉ ልሰበስብ እመጣለሁ፤ እነርሱም መጥተው ክብሬንም ያያሉ።

19 “በመካከላቸው ምልክት አደርጋለሁ፤ ከእነርሱም የተረፉትን አንዳንዶቹን ወደ አሕዛብ ወደ ተርሴስ፣ ወደ ፉጥ፣ ወደ ታወቁት ቀስተኞች ወደ ሉድ፣ ወደ ቶቤልና ያዋን እንዲሁም ዝናዬን ወዳልሰሙትና ክብሬን ወዳላዩት ራቅ ወዳሉት ደሴቶች እልካቸዋለሁ፤ በሕዝቦችም መካከል ክብሬን ይናገራሉ።

20 ለእግዚአብሔር ቍርባን እንዲሆኑ ወንድሞቻችሁን ሁሉ ከየመንግሥታቱ ወደ ተቀደሰው ተራራዬ ወደ ኢየሩሳሌም በፈረስ፣ በሠረገላና በጋሪ፣ በበቅሎና በግመል ያመጧቸዋል” ይላል እግዚአብሔር። “እስራኤላውያን የእህል ቍርባናቸውን በሥርዐቱ መሠረት በነጹ ዕቃዎች ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደሚያቀርቡ እነዚህንም ያቀርቧቸዋል።

21 እኔም ካህናትና ሌዋውያን ይሆኑ ዘንድ አንዳንዶቹን እመርጣቸዋለሁ” ይላል እግዚአብሔር።

22 “እኔ የምሠራቸው አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር በፊቴ ጸንተው እንደሚኖሩ፣ የእናንተና የዘራችሁ ስም እንደዚሁ ጸንቶ ይኖራል” ይላል እግዚአብሔር፤

23 “ከአንዱ ወር መባቻ እስከ ሌላው፣ እንዲሁም ከአንዱ ሰንበት እስከ ሌላው፣ የሰው ልጅ ሁሉ በፊቴ ሊሰግድ ይመጣል” ይላል እግዚአብሔር፤

24 “ወጥተውም በእኔ ላይ ያመፁትን ሰዎች ሬሳ ያያሉ፤ የሚበሏቸው ትሎች አይሞቱም፤ የሚያቃጥላቸው እሳታቸው አይጠፋም፤ ለሰውም ዘር ሁሉ አስጸያፊ ይሆናሉ።”

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告