Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ኢሳይያስ 61 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


የተወደደው የ እግዚአብሔር ዓመት

1 የጌታ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድኾች ወንጌልን እንድሰብክ፣ እግዚአብሔር ቀብቶኛልና። ልባቸው የተሰበረውን እንድጠግን፣ ለምርኮኞች ነጻነትን፣ ለእስረኞች መፈታትን እንዳውጅ ልኮኛል።

2 የተወደደችውንም የእግዚአብሔርን ዓመት፣ የአምላካችንንም የበቀል ቀን እንዳውጅ፣ የሚያለቅሱትን ሁሉ እንዳጽናና ልኮኛል፤

3 በጽዮን ያዘኑትን እንዳረጋጋ፣ በዐመድ ፈንታ፣ የውበት አክሊል እንድደፋላቸው፣ በልቅሶ ፈንታ፣ የደስታ ዘይት በራሳቸው ላይ እንዳፈስስላቸው፣ በትካዜ መንፈስ ፈንታ፣ የምስጋና መጐናጸፊያ እንድደርብላቸው ልኮኛል፤ እነርሱም የክብሩ መግለጫ እንዲሆኑ፣ እግዚአብሔር የተከላቸው፣ የጽድቅ ዛፎች ተብለው ይጠራሉ።

4 የጥንት ፍርስራሾችን መልሰው ይሠራሉ፤ በቀድሞ ጊዜ የወደሙትን መልሰው ያቆማሉ፤ ከብዙ ትውልድ በፊት የወደሙትን ፍርስራሽ ከተሞች እንደ ገና ይሠራሉ።

5 መጻተኞች የበግ መንጎቻችሁን ያግዳሉ፤ ባዕዳን በዕርሻችሁና በወይን ተክል ቦታችሁ ላይ ይሠሩላችኋል።

6 እናንተም የእግዚአብሔር ካህናት ተብላችሁ ትጠራላችሁ፤ የአምላካችን ባሮች ትባላላችሁ፤ የመንግሥታትን ሀብት ትመገባላችሁ፤ በብልጽግናቸውም ትኰራላችሁ።

7 ሕዝቤ በኀፍረታቸው ፈንታ፣ ዕጥፍ ይቀበላሉ፤ በውርደታቸው ፈንታ፣ በርስታቸው ደስ ይላቸዋል፤ የምድራቸውንም ዕጥፍ ርስት ይወርሳሉ፤ ዘላለማዊ ደስታም የእነርሱ ይሆናል።

8 “እኔ እግዚአብሔር ፍትሕን ስለምወድድ፣ ዝርፊያንና በደልን እጠላለሁ፤ በታማኝነቴም የሚገባቸውን እሰጣቸዋለሁ፤ ከእነርሱም ጋራ የዘላለም ኪዳን አደርጋለሁ።

9 ዘሮቻቸው በመንግሥታት፣ ልጆቻቸውም በሕዝቦች ዘንድ የታወቁ ይሆናሉ፤ የሚያዩአቸውም ሁሉ፣ እግዚአብሔር የባረካቸው ሕዝብ እንደ ሆኑ ያውቃሉ።”

10 በእግዚአብሔር እጅግ ደስ ይለኛል፤ ነፍሴ በአምላኬ ሐሤት ታደርጋለች፤ ሙሽራ ራሱን እንደሚያሳምር፣ ሙሽራዪቱም በዕንቈቿ እንደምታጌጥ፣ የድነትን ልብስ አልብሶኛል፤ የጽድቅንም መጐናጸፊያ ደርቦልኛል።

11 ምድር ቡቃያ እንደምታበቅል፣ የተክል ቦታ ችግኝ እንደሚያፈላ፣ ጌታ እግዚአብሔርም በመንግሥታት ሁሉ ፊት፣ ጽድቅንና ምስጋናን ያበቅላል።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告