ኢሳይያስ 56 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምለሌሎች የተሰጠ ድነት 1 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ፍትሕን ጠብቁ፤ መልካሙን አድርጉ፤ ማዳኔ በቅርብ ነው፤ ጽድቄም ፈጥኖ ይገለጣልና። 2 ሰንበትን ሳያረክስ የሚያከብር፣ ክፉን ከማድረግ እጁን የሚሰበስብ፣ የሚገታ፣ እነዚህን የሚፈጽም ሰው ብፁዕ ነው።” 3 ወደ እግዚአብሔር የተጠጋ መጻተኛ፣ “እግዚአብሔር በርግጥ ከሕዝቡ ይለየኛል” አይበል፤ ጃንደረባም፣ “እኔ ደረቅ ዛፍ ነኝ” አይበል። 4 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ሰንበቶቼን ለሚያከብሩ ጃንደረቦች፣ ደስ የሚያሠኘኝን ለሚመርጡ፣ ቃል ኪዳኔን፣ ለሚጠብቁ 5 በቤተ መቅደሴና በቅጥሮቼ ውስጥ፣ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች የበለጠ፣ መታሰቢያና ስም እሰጣቸዋለሁ፤ ለዘላለም፣ የማይጠፋ ስም እሰጣቸዋለሁ። 6 እርሱን ለማገልገል፣ ራሳቸውን ከእግዚአብሔር ጋራ ያቈራኙ መጻተኞች፣ የእግዚአብሔርን ስም በመውደድ፣ እርሱንም በማምለክ፣ ሰንበትን ሳያረክሱ የሚያከብሩትን ሁሉ፣ ቃል ኪዳኔንም የሚጠብቁትን፣ 7 ወደ ተቀደሰው ተራራዬ አመጣቸዋለሁ፤ በጸሎት ቤቴም ውስጥ ደስ አሰኛቸዋለሁ። የሚቃጠል መሥዋዕታቸውንና ሌሎች መሥዋዕቶቻቸውን፣ በመሠዊያዬ ቢሠዉ እቀበላቸዋለሁ፤ ቤቴ፣ ለሕዝቦች ሁሉ የጸሎት ቤት ተብሎ ይጠራልና።” 8 የተበተኑትን እስራኤል የሚሰበስብ፣ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ከተሰበሰቡት በተጨማሪ፣ ሌሎችን እንደ ገና እሰበስባለሁ።” በክፉዎች ላይ የእግዚአብሔር ወቀሣ 9 እናንተ የምድር አራዊት ሁሉ ኑ፤ እናንተ የዱር አራዊት ሁሉ ኑና በጥርሳቸሁ ቦጫጭቁ! 10 የእስራኤል ጠባቂዎች ዕውሮች ናቸው፤ ዕውቀት የላቸውም፤ ሁሉም ድምፅ የለሽ ውሾች ናቸው፤ መጮኽ አይችሉም፤ ተጋድመው ያልማሉ፤ እንቅልፍ ይወድዳሉ። 11 እጅግ ሲበዛ ሆዳም ውሾች ናቸው፤ ጠገብሁን አያውቁም፤ የማያስተውሉ እረኞች ናቸው፤ ሁሉም በየራሳቸው መንገድ ሄዱ፤ እያንዳንዳቸውም የግል ጥቅማቸውን ፈለጉ። 12 እርስ በርሳቸውም፣ “ኑና የወይን ጠጅ እንገባበዝ፤ እስክንሰክር እንጠጣ፤ ነገም ያው እንደ ዛሬ፣ ምናልባትም የተሻለ ቀን ይሆንልናል” ይባባላሉ። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.