ኢሳይያስ 50 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምየእስራኤል ኀጢአትና የ እግዚአብሔር ባሪያ ታዛዥነት 1 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እናታችሁን የፈታሁበት የፍች ወረቀት የት አለ? ወይስ እናንተን የሸጥኋችሁ ለየትኛው አበዳሪዬ ነው? እነሆ፤ ስለ ኀጢአታችሁ ተሸጣችኋል፤ ስለ መተላለፋችሁም እናታችሁ ተፈትታለች። 2 በመጣሁ ጊዜ ለምን በዚያ ሰው አልነበረም? በተጣራሁስ ጊዜ የሚመልስ ሰው እንዴት በዚያ ታጣ? ስለ እናንተ ወጆ ለመክፈል ክንዴ ዐጥራ ነበርን? እናንተንስ ለማዳን ኀይል አነሰኝን? እነሆ፤ በተግሣጼ ባሕሩን አደርቃለሁ፤ ወንዞችን ምድረ በዳ አደርጋለሁ፤ ዓሦቻቸው ውሃ በማጣት ይሸታሉ፤ በጥማትም ይሞታሉ። 3 ሰማይን ጨለማ አለብሰዋለሁ፤ ማቅን መሸፈኛው አደርጋለሁ።” 4 ልዑል እግዚአብሔር የተባ አንደበት ሰጥቶኛል፤ ስለዚህ ደካሞችን ብርቱ ለማድረግ ምን ማለት እንዳለብኝ ዐውቃለሁ፤ በየማለዳው ያነቃኛል፤ በመማር ላይ እንዳለ ተማሪ ለመስማት ጆሮዬን ያነቃዋል። 5 ልዑል እግዚአብሔር ጆሮዬን ከፍቶታል፤ እኔም ዐመፀኛ አይደለሁም፤ ወደ ኋላም አላፈገፈግሁም። 6 ለሚገርፉኝ ጀርባዬን፣ ጢሜን ለሚነጩ ጕንጬን ሰጠሁ፤ ፊቴን ከውርደት፣ ከጥፋትም አልሰወርሁም። 7 ጌታ እግዚአብሔር ስለሚረዳኝ አልዋረድም፤ ስለዚህ ፊቴን እንደ ባልጩት ድንጋይ አድርጌአለሁ፤ እንደማላፍርም ዐውቃለሁ። 8 የሚያጸድቀኝ በአጠገቤ አለ፤ ታዲያ ማን ሊከስሰኝ ይችላል? እስኪ ፊት ለፊት እንጋጠም! ተቃዋሚዬስ ማን ነው? እስኪ ይምጣ! 9 የሚረዳኝ እርሱ ጌታ እግዚአብሔር ነው፤ የሚፈርድብኝስ ማን ነው? እነሆ፤ ሁሉም እንደ ልብስ ያረጃሉ፤ ብልም ይበላቸዋል። 10 ከእናንተ እግዚአብሔርን የሚፈራ፣ የባሪያውንም ቃል የሚሰማ ማን ነው? ያ ሰው በጨለማ የሚሄድ ከሆነና፣ ብርሃንም ከሌለው፣ በእግዚአብሔር ስም ይታመን፤ በአምላኩም ይደገፍ። 11 አሁን ግን እናንተ እሳት አንድዳችሁ፣ የራሳችሁን የሚንቦገቦግ ችቦ የያዛችሁ ሁሉ፣ በሉ በእሳታችሁ ብርሃን ሂዱ፤ ባንቦገቦጋችሁትም የችቦ ብርሃን ተመላለሱ። እንግዲህ ከእጄ የምትቀበሉት ይህ ነው፤ በሥቃይም ትጋደማላችሁ። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.