Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ኢሳይያስ 46 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


የባቢሎን አማልክት

1 ቤል ተዋረደ፤ ናባው እጅግ ዝቅ አለ፤ ጣዖቶቻቸው በአጋሰስ ተጭነዋል፤ ይዘዋቸው የሚዞሩት ምስሎች ሸክም ናቸው፤ ለደከሙ እንስሳት ከባድ ጭነት ናቸው።

2 እነርሱም በአንድ ላይ ዝቅ ይላሉ፤ ያጐነብሳሉ፤ ጭነቱን ለማዳን አይችሉም፤ ራሳቸውም በምርኮ ይወሰዳሉ።

3 “እናንተ የያዕቆብ ቤት ሆይ፤ የእስራኤል ቤት ቅሬታ ሁሉ፣ ከተፀነሳችሁበት ጊዜ ጀምሮ የያዝኋችሁ፣ ከተወለዳችሁበት ጊዜ ጀምሮ የተሸከምኋችሁ ስሙኝ።

4 እስከ ሽምግልናችሁ፣ እስከ ሽበትም፣ የምሸከማችሁ እኔ ነኝ፤ እኔው ነኝ። ሠርቻችኋለሁ፤ እሸከማችኋለሁ፤ እደግፋችኋለሁ፤ አድናችኋለሁ።

5 “ከማን ጋራ ታወዳድሩኛላችሁ? ከማንስ ጋራ እኩል ታደርጉኛላችሁ? እንመሳሰልስ ዘንድ ከማን ጋራ ታነጻጽሩኛላችሁ?

6 ሰዎች ወርቅ ከከረጢታቸው ይዘረግፋሉ፤ ብርንም በሚዛን ይመዝናሉ፤ አንጥረኛን ይቀጥራሉ፤ እርሱም አምላክ አድርጎ ያበጅላቸዋል። እነርሱም ይሰግዱለታል፤ ያመልኩታልም።

7 አንሥተው በትከሻቸው ይሸከሙታል፤ እቦታው ያደርጉታል፤ በዚያም ይቆማል፤ ከዚያም ቦታ አይንቀሳቀስም፤ ማንም ወደ እርሱ ቢጮኽ አይመልስም፤ ከጭንቀቱም አያድነውም።

8 “እናንተ በደለኞች፣ ይህን አስታውሱ፤ አስቡበትም፤ በልባችሁም ያዙት።

9 የጥንቱን፣ የቀደመውን ነገር አስታውሱ፤ እኔ አምላክ ነኝ፤ ከእኔም በቀር ሌላ የለም፤ እኔ አምላክ ነኝ፤ እንደ እኔ ያለ የለም።

10 የመጨረሻውን ከመጀመሪያው፣ ገና የሚመጣውንም ከጥንቱ ተናግሬአለሁ፤ ‘ምክሬ የጸና ነው፤ ደስ የሚያሠኘኝንም ሁሉ አደርጋለሁ’ እላለሁ።

11 ከምሥራቅ ነጣቂ አሞራ፣ ከሩቅ ምድር ዐላማዬን የሚፈጽም ሰው እጠራለሁ። የተናገርሁትን አደርጋለሁ፤ ያቀድሁትን እፈጽማለሁ።

12 እናንተ ልበ ደንዳኖች፣ ከጽድቅም የራቃችሁ ስሙኝ።

13 ጽድቄን እያመጣሁ ነው፤ ሩቅም አይደለም፤ ማዳኔም አይዘገይም። ለጽዮን ድነትን፣ ለእስራኤል ክብሬን አጐናጽፋለሁ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告