Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ኢሳይያስ 45 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም

1 “ለቀባሁት፣ ቀኝ እጁን ለያዝሁት፣ ነገሥታትን ትጥቅ አስፈታ ዘንድ፣ ሕዝብን ሁሉ ላስገዛለት፣ ደጆች እንዳይዘጉ፣ በሮቹን በፊቱ ለምከፍትለት፣ ለቂሮስ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤

2 ‘በፊትህ እሄዳለሁ፤ ተራሮችን እደለድላለሁ፤ የናስ በሮችን እሰብራለሁ፤ የብረት መወርወሪያዎችንም እቈርጣለሁ።

3 በስምህ የምጠራህ የእስራኤል አምላክ፣ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቅ ዘንድ፣ በተሰወረ ስፍራ የተከማቸውን ሀብት፣ በጨለማም ያለውን ንብረት እሰጥሃለሁ።

4 ስለ ባሪያዬ ስለ ያዕቆብ፣ ስለ መረጥሁት ስለ እስራኤል፣ አንተ ባታውቀኝ እንኳ፣ በስምህ ጠርቼሃለሁ፤ የክብርም ስም ሰጥቼሃለሁ።

5 እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከእኔ ሌላ ማንም የለም፤ ከእኔ በቀር አምላክ የለም። አንተ ባታውቀኝም እንኳ፣ እኔ አበረታሃለሁ።

6 ይኸውም ሰዎች ከፀሓይ መውጫ፣ እስከ መጥለቂያው፣ ከእኔ በቀር ሌላ እንደሌለ እንዲያውቁ ነው፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከእኔ ሌላ ማንም የለም።

7 እኔ ብርሃንን ሠራሁ፤ ጨለማንም ፈጠርሁ፤ አበለጽጋለሁ፤ አደኸያለሁ፤ ይህን ሁሉ የማደርግ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።’

8 “እናንተ ሰማያት፣ ጽድቅን ከላይ አዝንቡ፤ ደመናትም ወደ ታች አንጠብጥቡ፤ ምድር ትከፈት፤ ድነት ይብቀል፤ ጽድቅም ዐብሮት ይደግ፤ እኔ እግዚአብሔር ፈጥሬዋለሁ።

9 “ከዐፈር ሸክላዎች መካከል፣ ከሠሪው ጋራ ክርክር ለሚገጥም ወዮለት! ጭቃ፣ ሸክላ ሠሪውን፣ ‘ምን እየሠራህ ነው?’ ይለዋልን? የምትሠራውስ ሥራ፣ ‘እጅ የለህም’ ይልሃልን?

10 አባቱን፣ ‘የወለድኸው ምንድን ነው?’ ለሚል፣ እናቱንም፣ ‘ምን ወለድሽ?’ ለሚል ወዮለት!

11 “የእስራኤል ቅዱስ፣ ሠሪውም የሆነ እግዚአብሔር፣ ስለሚመጡ ነገሮች እንዲህ ይላል፤ ‘ስለ ልጆቼ ትጠይቁኛላችሁን? ስለ እጆቼስ ሥራ ታዝዙኛላችሁን?

12 ምድርን የሠራሁ እኔ ነኝ፤ ሰውንም በላይዋ ፈጥሬአለሁ፤ እጆቼ ሰማያትን ዘርግተዋል፤ የሰማይንም ሰራዊት አሰማርቻለሁ።

13 ቂሮስን በጽድቅ አስነሥቻለሁ፤ መንገዱን ሁሉ አስተካክዬለታለሁ፤ ከተማዬን እንደ ገና ይሠራታል፤ ምርኮኞቼን ያለ ክፍያ ወይም ያለ ዋጋ፣ ነጻ ያወጣል፤’ ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።”

14 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “የግብጽ ሀብትና የኢትዮጵያ ንግድ፣ ቁመተ ረዣዥሞቹ የሳባ ሰዎች፣ ወደ አንተ ይመጣሉ፤ የአንተ ይሆናሉ፤ ከኋላ ይከተሉሃል፤ በሰንሰለትም ታስረው ወደ አንተ በመምጣት፣ በፊትህ እየሰገዱ፣ ‘በእውነት እግዚአብሔር ከአንተ ጋራ ነው፤ ከርሱም በቀር ሌላ አምላክ የለም’ ብለው ይለምኑሃል።”

15 አዳኙ የእስራኤል አምላክ ሆይ፤ አንተ በእውነት ራስህን የምትሰውር አምላክ ነህ።

16 የእጅ ጥበብ ባለሙያዎች ሁሉ ያፍራሉ፤ ይቀልላሉ፤ በአንድነት ይዋረዳሉ።

17 እስራኤል ግን በእግዚአብሔር፣ በዘላለም ድነት ይድናል፤ እናንተም ለዘላለም፣ አታፍሩም፤ አትዋረዱም።

18 ሰማያትን የፈጠረ፣ እርሱ እግዚአብሔር ነው፤ ምድርን ያበጃት፣ የሠራት፣ የመሠረታት፣ የሰው መኖሪያ እንጂ፣ ባዶ እንድትሆን ያልፈጠራት፣ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤ “እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከእኔም በቀር ሌላ የለም።

19 በጨለማ ምድር፣ በምስጢር አልተናገርሁም፤ ለያዕቆብም ዘር፣ ‘በከንቱ ፈልጉኝ’ አላልሁም። እኔ እግዚአብሔር ጽድቅን እናገራለሁ፤ ትክክለኛውንም ነገር ዐውጃለሁ።

20 “በአንድነት ተሰብሰቡ፤ ቅረቡም፤ እናንተ ከአሕዛብ የኰበለላችሁ፣ ኑ። የዕንጨት ጣዖት የሚሸከሙ፣ ማዳን ወደማይችል አምላክ የሚጸልዩ፣ ዕውቀት የላቸውም።

21 ጕዳያችሁን ተናገሩ፤ አቅርቡ፤ ተሰብስበውም ይማከሩ። ይህን አስቀድሞ ማን ዐወጀ? ከጥንትስ ማን ተናገረ? እኔ እግዚአብሔር አይደለሁምን? ጻድቅና አዳኝ የሆነ አምላክ፣ ከእኔ በቀር ማንም የለም፤ ከእኔ ሌላ አምላክ የለም።

22 “እናንተ የምድር ዳርቻ ሁሉ፣ እኔ አምላክ ነኝ፤ ከእኔም በቀር ሌላ የለምና፤ ትድኑ ዘንድ ወደ እኔ ተመለሱ።

23 ጕልበት ሁሉ ለእኔ ይንበረከካል፤ ምላስም ሁሉ በእኔ ይምላል፤ ብዬ በራሴ ምያለሁ፤ የማይታጠፍ ቃል፣ ከአፌ በጽድቅ ወጥቷል።

24 ስለ እኔም ሲናገሩ፣ ‘ጽድቅና ኀይል፣ በእግዚአብሔር ብቻ ነው’ ይላሉ።” በርሱ ላይ በቍጣ የተነሡ ሁሉ፣ ወደ እርሱ መጥተው ያፍራሉ።

25 ነገር ግን የእስራኤል ዘር ሁሉ፣ በእግዚአብሔር ይጸድቃሉ፤ ሞገስንም ያገኛሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告