Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ኢሳይያስ 40 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


የ እግዚአብሔር ን ሕዝብ የሚያጽናና ቃል

1 አጽናኑ፤ ሕዝቤን አጽናኑ፤ ይላል አምላካችሁ።

2 ለኢየሩሳሌም አለዝባችሁ ንገሯት፤ ዐውጁላትም፤ በባርነት ያገለገለችበት ዘመን አብቅቷል፤ የኀጢአቷም ዋጋ ተከፍሏል፤ ስለ ኀጢአቷ ሁሉ ከእግዚአብሔር እጅ ሁለት ዕጥፍ ተቀብላለች።

3 የዐዋጅ ነጋሪ ድምፅ እንዲህ ይላል፤ “በምድረ በዳ የጌታን መንገድ፣ አዘጋጁ፤ ለአምላካችን አውራ ጐዳና፣ በበረሓ አስተካክሉ።

4 ሸለቆው ሁሉ ከፍ ይላል፤ ተራራውና ኰረብታው ሁሉ ዝቅ ይላል፤ ጠማማው ምድር ይስተካከላል፤ ወጣ ገባውም ለጥ ያለ ሜዳ ይሆናል።

5 የእግዚአብሔርም ክብር ይገለጣል፤ የሰውም ዘር ሁሉ በአንድነት ያየዋል፤ የእግዚአብሔር አፍ ይህን ተናግሯልና።”

6 ድምፅም፣ “ጩኽ” አለኝ፤ እኔም፣ “ምን ብዬ ልጩኽ?” አልሁ። “ሰው ሁሉ እንደ ሣር ነው፤ ክብሩም ሁሉ እንደ ሜዳ አበባ ነው።

7 ሣሩ ይደርቃል፤ አበባውም ይረግፋል፤ የእግዚአብሔር እስትንፋስ ነፍሶበታልና፤ ሕዝቡ በርግጥ ሣር ነው።

8 ሣሩ ይደርቃል፤ አበባውም ይረግፋል፤ የአምላካችን ቃል ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።”

9 አንተ ለጽዮን የምሥራችን የምትነግር፤ ከፍ ወዳለው ተራራ ውጣ፤ አንተ ለኢየሩሳሌም ብሥራት የምትነግር፣ ድምፅህን በኀይል ከፍ አድርገህ ጩኽ። ከፍ አድርገው፤ አትፍራ፤ ለይሁዳም ከተሞች፣ “እነሆ፤ አምላካችሁ!” በል።

10 እነሆ፤ ጌታ እግዚአብሔር በኀይል ይመጣል፤ ክንዱ ስለ እርሱ ይገዛል። እነሆ፤ ዋጋው ከርሱ ጋራ ነው፤ የሚከፍለውም ብድራት ዐብሮት አለ።

11 መንጋውን እንደ እረኛ ያሰማራል፤ ጠቦቶቹን በክንዱ ይሰበስባል፤ በዕቅፉም ይይዛቸዋል፤ የሚያጠቡትንም በጥንቃቄ ይመራል።

12 ውሆችን በዕፍኙ የሰፈረ፣ ሰማያትን በስንዝሩ የለካ፣ የምድርን ዐፈር በመስፈሪያ ሰብስቦ የያዘ፣ ተራሮችን በሚዛን፣ ኰረብቶችንም በመድሎት የመዘነ ማነው?

13 የእግዚአብሔርን መንፈስ የተረዳ፣ አማካሪውስ ሆኖ ያስተማረው ማን ነው?

14 ዕውቀት ለማግኘት እግዚአብሔር ማንን አማከረ? ትክክለኛውንስ መንገድ ማን አስተማረው? ዕውቀትን ያስተማረው፣ የማስተዋልንም መንገድ ያሳየው ማን ነበር?

15 እነሆ፤ አሕዛብ በገንቦ ውስጥ እንዳለች ጠብታ ናቸው፤ በሚዛን ላይ እንዳለ ትቢያ ይቈጠራሉ፤ ደሴቶችንም እንደ ደቃቅ ዐፈር ይመዝናቸዋል።

16 ሊባኖስ ለመሠዊያ እሳት አትበቃም፤ የእንስሶቿም ቍጥር ለሚቃጠል መሥዋዕት ያንሳል።

17 አሕዛብ ሁሉ በፊቱ እንደ ኢምንት ናቸው፤ ከምንም የማይቈጠሩ መና ናቸው።

18 እንግዲህ፣ እግዚአብሔርን ከማን ጋራ ታወዳድሩታላችሁ? ከየትኛውስ ምስል ጋራ ታነጻጽሩታላችሁ?

19 የተቀረጸውንማ ምስል የእጅ ጥበብ ባለሙያ ይቀርጸዋል፤ ወርቅ አንጥረኛም በወርቅ ይለብጠዋል፤ የብር ሰንሰለትም ያበጅለታል።

20 እንዲህ ያለውን መባ ማቅረብ የማይችል ምስኪን ድኻ፣ የማይነቅዝ ዕንጨት ይመርጣል፤ የማይወድቅ ምስልን ለማቆምም፣ ታዋቂ የእጅ ጥበብ ባለሙያ ይፈልጋል።

21 አላወቃችሁምን? አልሰማችሁምን? ከጥንት አልተነገራችሁምን? ምድር ከተመሠረተች ጀምሮ አላስተዋላችሁምን?

22 እርሱ ከምድር ክበብ በላይ በዙፋን ላይ ይቀመጣል፤ ሕዝቦቿም እንደ አንበጣ ናቸው። ሰማያትን እንደ ድባብ ይዘረጋቸዋል፤ እንደ መኖሪያ ድንኳንም ይተክላቸዋል።

23 አለቆችን ኢምንት፣ የዚህን ዓለም ገዦች እንዳልነበሩ ያደርጋቸዋል።

24 ተተክለው ምንም ያህል ሳይቈዩ፣ ተዘርተው ምንም ያህል ሳይሰነብቱ፣ ገና ሥር መስደድ ሳይጀምሩ አነፈሰባቸው፤ እነርሱም ደረቁ፤ ዐውሎ ነፋስም እንደ ገለባ ጠራርጎ ወሰዳቸው።

25 ቅዱሱ፣ “ከማን ጋራ ታወዳድሩኛላችሁ? የሚስተካከለኝስ ማን አለ?” ይላል።

26 ዐይናችሁን አንሡ፤ ወደ ሰማይ ተመልከቱ፤ እነዚህን ሁሉ የፈጠረ ማን ነው? የከዋክብትን ሰራዊት አንድ በአንድ የሚያወጣቸው፣ በየስማቸው የሚጠራቸው እርሱ ነው። ከኀይሉ ታላቅነትና ከችሎታው ብርታት የተነሣ፣ አንዳቸውም አይጠፉም።

27 ያዕቆብ ሆይ፤ ለምን እንዲህ ትላለህ? እስራኤል ሆይ፤ ለምን እንዲህ ትናገራለህ? “መንገዴ ከእግዚአብሔር ተሰውራለች፤ ፍርዴም በአምላኬ ቸል ተብላለች” ለምን ትላለህ?

28 አታውቅምን? አልሰማህምን? እግዚአብሔር የዘላለም አምላክ፣ የምድር ዳርቻ ፈጣሪ ነው። አይደክምም፤ አይታክትም፤ ማስተዋሉም በማንም አይመረመርም።

29 ለደከመው ብርታት ይሰጣል፤ ለዛለው ጕልበት ይጨምራል።

30 ወጣቶች እንኳ ይደክማሉ፤ ይታክታሉም፤ ጐበዛዝትም ተሰናክለው ይወድቃሉ።

31 እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ግን፣ ኀይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስር በክንፍ ይወጣሉ፤ ይሮጣሉ፤ አይታክቱም፤ ይሄዳሉ፤ አይደክሙም።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告