Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ኢሳይያስ 38 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


የሕዝቅያስ መታመም

1 በዚያ ጊዜ ሕዝቅያስ በጠና ታምሞ፤ ሊሞት ተቃርቦ ነበር። የአሞጽ ልጅ ነቢዩ ኢሳይያስም ወደ እርሱ መጥቶ፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ከሕመምህ አትድንም፤ ትሞታለህና ቤትህን አስተካክል’ ” አለው።

2 ሕዝቅያስም ፊቱን ወደ ግድግዳ አዙሮ፣ እንዲህ ሲል ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤

3 “እግዚአብሔር ሆይ፤ በፊትህ በታማኝነትና በፍጹም ልብ እንደ ሄድሁ፤ ደስ የሚያሰኝህንም እንዳደረግሁ ዐስብ።” ሕዝቅያስም አምርሮ አለቀሰ።

4 የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ኢሳይያስ እንዲህ ሲል መጣ፤

5 “ሂድና ለሕዝቅያስ እንዲህ ብለህ ንገረው፤ ‘የአባትህ የዳዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ጸሎትህን ሰምቻለሁ፤ እንባህንም አይቻለሁ፤ በዕድሜህም ላይ ዐሥራ ዐምስት ዓመት እጨምርልሃለሁ።

6 አንተንና ይህችን ከተማ ከአሦር ንጉሥ እጅ እታደጋለሁ፤ ይህችን ከተማ እከላከልላታለሁ።

7 “ ‘እግዚአብሔር የገባልህን ቃል እንደሚፈጽምልህ፣ የእግዚአብሔር ምልክት ይህ ነው፤

8 በአካዝ የሰዓት መቍጠሪያ ደረጃ ላይ፣ የወረደውን የፀሓይ ጥላ በዐሥር ደረጃ ወደ ኋላ እንዲመለስ አደርጋለሁ።’ ” ስለዚህ ወርዶ የነበረው የፀሓይ ጥላ ያንኑ ያህል ወደ ኋላ ተመለሰ።

9 የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ ከሕመሙ ከተፈወሰ በኋላ የጻፈው ጽሕፈት፤

10 እኔ፣ “በዕድሜዬ እኩሌታ፣ በሲኦል ደጆች ማለፍ አለብኝን? የቀረውንስ ዘመኔን ልነጠቅ ይገባልን?” አልሁ።

11 እንዲህም አልሁ፤ “ዳግም እግዚአብሔርን፣ እግዚአብሔርን በሕያዋን ምድር አላይም፤ ከእንግዲህም የሰውን ዘር አላይም፤ በዚህ ዓለም ከሚኖሩትም ጋራ አልሆንም።

12 ቤቴ እንደ እረኛ ድንኳን ተነቀለ፤ ከእኔም ተወሰደ፤ ሕይወቴን እንደ ሸማኔ ጠቀለልሁ፤ ከመጠቅለያ ቈርጦኛል፤ ከጧት እስከ ማታ ልትጨርሰኝ ፈጠንህ።

13 እስከ ማለዳ በትዕግሥት ጠበቅሁ፤ እርሱ ግን እንደ አንበሳ ዐጥንቶቼን ሁሉ ሰባበረ፤ ከጧት እስከ ማታም ልትጨርሰኝ ፈጠንህ።

14 እንደ ጨረባ፣ እንደ ሽመላም ተንጫጫሁ፤ እንደ ርግብ አልጐመጐምሁ፤ ዐይኖቼ ወደ ሰማይ በመመልከት ደከሙ፤ ጌታ ሆይ፤ ተጨንቄአለሁና ታደገኝ!”

15 እንግዲህ ምን እላለሁ? እርሱ ተናግሮኛል፤ ራሱ ደግሞ ይህን አድርጓል፤ ስለ ነፍሴ ጭንቀት፣ ዕድሜዬን ሁሉ በትሕትና እሄዳለሁ።

16 ጌታ ሆይ፤ ሰዎች በእነዚህ ነገሮች ይኖራሉ፤ መንፈሴም እንዲሁ በእነዚህ ሕይወትን ያገኛል፤ ፈወስኸኝ፤ በሕይወትም አኖርኸኝ።

17 እነሆ፤ በሥቃይ የተጨነቅሁት፣ ለጥቅሜ ሆነ፤ ከጥፋት ጕድጓድ፣ በፍቅርህ ጠበቅኸኝ፤ ኀጢአቴንም ሁሉ፣ ወደ ኋላህ ጣልህ።

18 ሲኦል አያመሰግንህም፤ ሞት አያወድስህም፤ ወደ ጕድጓድ የሚወርዱ፣ የአንተን ታማኝነት ተስፋ አያደርጉም።

19 እኔ ዛሬ እንደማደርገው፣ ሕያዋን እነርሱ ያመሰግኑሃል። ስለ አንተ ታማኝነትም፣ አባቶች ለልጆቻቸው ይነግራሉ።

20 እግዚአብሔር ያድነኛል፤ ስለዚህ በዕድሜ ዘመናችን ሁሉ፣ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ፣ አውታር ባለው መሣሪያ እንዘምራለን።

21 ኢሳይያስም፣ “የበለስ ጥፍጥፍ ወስዳችሁ በዕባጩ ላይ አድርጉለት፤ እርሱም ይፈወሳል” ብሎ ነበር።

22 ሕዝቅያስም፣ “ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እወጣ ዘንድ ምልክቱ ምንድን ነው?” ብሎ ነበር።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告