Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ኢሳይያስ 33 - አዲሱ መደበኛ ትርጒም


የጭንቅ ጊዜና ርዳታ

1 አንተ ሳትጠፋ የምታጠፋ፣ አንት አጥፊ፣ ወዮልህ! አንተ ሳትካድ የምትክድ፣ አንት ከዳተኛ፣ ወዮልህ! ማጥፋትን በተውህ ጊዜ፣ ትጠፋለህ፤ ክሕደትህንም በተውህ ጊዜ ትከዳለህ።

2 እግዚአብሔር ሆይ፤ ማረን፤ አንተን ተስፋ አድርገናል። በየማለዳው ብርታት፣ በጭንቅ ጊዜም ድነት ሁነን።

3 ሕዝቦች በድምፅህ ነጐድጓድ ይሸሻሉ፤ መንግሥታት ስትነሣ ይበተናሉ።

4 ሕዝቦች ሆይ፤ አንበጣ እንደሚሰበስብ ብዝበዛችሁም ይሰበሰባል፤ ሰዎችም እንደ ኵብኵባ ይጨፍሩበታል።

5 እግዚአብሔር በአርያም ተቀምጧልና ከፍ ከፍ አለ፤ ጽዮንን በጽድቅና በፍትሕ ይሞላታል።

6 እርሱ ለዘመንህ የሚያስተማምን መሠረት፣ የድነት፣ የዕውቀትና የጥበብ መዝገብ ይሆናል፤ እግዚአብሔርንም መፍራት የዚህ ሀብት ቍልፍ ነው።

7 እነሆ፤ ጐበዞቻቸው በየመንገዱ ይጮኻሉ፤ የሰላም መልእክተኞችም አምርረው ያለቅሳሉ።

8 አውራ ጐዳናዎች ባዶ ናቸው፤ በመንገድ ላይ ሰው የለም፤ ስምምነቱ ፈርሷል፤ መካሪዎቹ ተንቀዋል፤ የሚከበርም የለም።

9 ምድሪቱ አለቀሰች፤ መነመነች፤ ሊባኖስ ዐፈረች፤ ጠወለገች፤ ሳሮን እንደ ዓረባ ምድረ በዳ ሆነች፤ ባሳንና ቀርሜሎስ ቅጠላቸውን አረገፉ።

10 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “አሁን እነሣለሁ፤ አሁን ከፍ ከፍ እላለሁ፤ አሁን እከብራለሁ።

11 ገለባን ፀነሳችሁ፤ እብቅንም ወለዳችሁ፤ እስትንፋሳችሁም የሚበላችሁ እሳት ነው።

12 ሕዝቦች ኖራ እንደሚወጣው ድንጋይ ይቃጠላሉ፤ እንደ እሾኽ ቍጥቋጦ በእሳት ይጋያሉ።”

13 እናንተ በሩቅ ያላችሁ ያደረግሁትን ስሙ፤ እናንተ በቅርብ ያላችሁ ኀይሌን ዕወቁ!

14 በጽዮን ያሉ ኀጢአተኞች ደነገጡ፤ አምላክ የሌላቸውም ፍርሀት ይዟቸው፣ “ከእኛ መካከል ከሚባላ እሳት ጋራ ማን መኖር ይችላል፣ ከዘላለም እሳትስ ጋራ ማን መኖር ይችላል?” አሉ።

15 በጽድቅ የሚራመድ፣ ቅን ነገር የሚናገር፣ በሽንገላ የሚገኝን ትርፍ የሚንቅ፣ መማለጃን ላለመቀበል እጁን የሚሰበስብ፣ የግድያን ሤራ ላለመስማት ጆሮውን የሚደፍን፣ ክፋትን ላለማየት ዐይኑን የሚጨፍን፣

16 ይህ ሰው በከፍታ ላይ ይኖራል፤ የተራራም ምሽግ መጠጊያው ይሆናል፤ እንጀራ ይሰጠዋል፣ ውሃውም አይቋረጥበትም።

17 ዐይኖችህ ንጉሡን በውበቱ ያዩታል፤ በሩቅ የተዘረጋችውንም ምድር ይመለከታሉ።

18 የቀደመው መከራ ትዝ እያለህ፣ “ያ ዋና አለቃ የት አለ? ግብር ተቀባዩስ ወዴት ሄደ? የመጠበቂያ ማማ ኀላፊውስ የት አለ?” ትላለህ።

19 እነዚያ ንግግራቸው የማይገባ፣ የሚሉትም የማይታወቅ፣ ሊረዱት የማይቻል ቋንቋ የሚናገሩትን ጋጠወጥ ሕዝብ ከእንግዲህ አታያቸውም።

20 በዓላታችንን የምናከብርባትን ከተማ ጽዮንን ተመልከት፤ ሰላማዊ መኖሪያ፣ የማትነቃነቅ ድንኳን የሆነችውን፣ ካስማዋ የማይነቀል፣ ከገመዷ አንዱ እንኳ የማይበጠሰውን፣ ኢየሩሳሌምን ዐይኖችህ ያያሉ።

21 እግዚአብሔር በዚያ ኀይላችን ይሆናል፤ ባለመቅዘፊያ ጀልባዎች እንደማያልፉባቸው፣ ታላላቅ መርከቦችም እንደማይሻገሯቸው፣ ሰፋፊ ወንዞችና ጅረቶች ይሆንልናል።

22 እግዚአብሔር ዳኛችን ነው፤ እግዚአብሔር ሕግ ሰጪያችን ነው፤ እግዚአብሔር ንጉሣችን ነው፤ የሚያድነንም እርሱ ነውና።

23 መወጠሪያ ገመድህ ላልቷል፤ ምሰሶው ጠብቆ አልተተከለም፤ ሸራው አልተወጠረም፤ በዚያ ጊዜ ታላቅ ምርኮ ይከፋፈላል፤ ዐንካሳ እንኳ ሳይቀር ምርኮ ይወስዳል።

24 በጽዮን ተቀምጦ፣ “ታምሜአለሁ” የሚል አይኖርም፤ በዚያ የሚኖሩ ሰዎች ኀጢአትም ይቅር ይባላል።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™

የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.

በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።

The Holy Bible, New Amharic Standard Version™

Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.

Used with permission. All rights reserved worldwide. 

Biblica, Inc.
跟着我们:



广告