ኢሳይያስ 31 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምበግብጽ ለሚደገፉ ወዮላቸው 1 ወደ እስራኤል ቅዱስ ለማይመለከቱ፣ ከእግዚአብሔርም ርዳታን ለማይሹ፣ ነገር ግን፤ ለርዳታ ብለው ወደ ግብጽ ለሚወርዱ፣ በፈረሶች ለሚታመኑ፣ በሠረገሎቻቸው ብዛት፣ በፈረሶቻቸውም ታላቅ ብርታት ለሚመኩ ወዮላቸው! 2 እርሱም ግን ጠቢብ ነው፤ ጥፋትን ያመጣል፤ ቃሉን አያጥፍም። በክፉ አድራጊዎች ቤት ላይ፣ በደለኞችንም በሚረዱ ላይ ይነሣል። 3 ግብጻውያን ሰዎች እንጂ አምላክ አይደሉም፤ ፈረሶቻቸውም ሥጋ እንጂ መንፈስ አይደሉም፤ እግዚአብሔር እጁን ሲዘረጋ፣ ርዳታ ሰጪው ይሰናከላል፤ ተረጂውም ይወድቃል፤ ሁለቱም በአንድ ላይ ይጠፋሉ። 4 እግዚአብሔር እንዲህ ብሎኛል፤ “አንበሳ ወይም የአንበሳ ደቦል የሰበረውን ይዞ ሲያገሣ፣ ብዙ እረኞች ተጠራርተው ሲመጡበት፣ ጩኸታቸው እንደማያስፈራው፣ በድምፃቸውም እንደማይታወክ፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር፣ በጽዮን ተራራና በከፍታዎቿ ላይ ለውጊያ እንዲሁ ይወርዳል። 5 በዐናት ላይ እንደሚያንዣብቡ ወፎች፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን እንዲሁ ይጋርዳታል፤ ይከልላታል፤ ይታደጋታል፤ በላይዋ ያልፋል፤ ያድናታልም።” 6 እናንተ እስራኤላውያን ሆይ፤ እጅግ ወዳመፃችሁበት ወደ እርሱ ተመለሱ። 7 በዚያ ቀን በኀጢአት የተሞላ እጃችሁ የሠራቸውን የወርቅና የብር ጣዖቶች ሁላችሁም ትጥላላችሁና። 8 “አሦር የሰው ባልሆነ ሰይፍ ይወድቃል፤ የሥጋ ለባሽ ያልሆነም ሰይፍ ይበላዋል። ከሰይፍ ፊት ይሸሻል፤ ጕልማሶቹም የግዳጅ ሥራ ይሠራሉ። 9 ጠንካራ ምሽጉ በሽብር ምክንያት ይወድቃል፤ መሪዎቹም የጦር ዐርማ ሲያዩ በድንጋጤ ይዋጣሉ” ይላል እሳቱ በጽዮን፣ ማንደጃውም በኢየሩሳሌም የሆነ እግዚአብሔር። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.