ኢሳይያስ 3 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምበኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ የሚመጣ ፍርድ 1 እነሆ፤ ጌታ፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከኢየሩሳሌምና ከይሁዳ ድጋፉንና ርዳታውን፣ የምግብና የውሃ ርዳታውን ሁሉ ይነሣል፤ 2 ጀግናውንና ተዋጊውን፣ ፈራጁንና ነቢዩን፣ አስማተኛውንና ሽማግሌውን፣ 3 የዐምሳ አለቃውንና ባለማዕርጉን፣ አማካሪውንና ጠቢቡን የእጅ ባለሙያ፣ ብልኁንም ምትሀተኛ ይነሣል። 4 “ልጆችን መሪዎቻቸው አደርጋለሁ፤ ያልበሰሉ ሕፃናትም ይገዟቸዋል።” 5 ሕዝብ እርስ በርሱ ይጨቋቈናል፤ ሰው በሰው ላይ፤ ባልንጀራ በባልንጀራው ላይ፣ ወጣቱ በሽማግሌው ላይ፣ ተራው ሰው በተከበረው ላይ ይነሣል። 6 ሰውም በአባቱ ቤት ከወንድሞቹ አንዱን ይዞ፣ “አንተ ልብስ ስላለህ መሪ ሁነን፤ ይህንም የፍርስራሽ ክምር ግዛ!” ይለዋል። 7 እርሱ ግን በዚያ ቀን ድምፁን ከፍ አድርጎ፣ “እኔ መፍትሒ አልሆንም፤ በቤቴም ልብስና ምግብ የለኝም፤ የሕዝብ መሪ አታድርጉኝ” ይላል። 8 ኢየሩሳሌም ተንገዳግዳለች፤ ይሁዳም ለመውደቅ ተቃርባለች፤ ንግግራቸውም ሆነ ድርጊታቸው እግዚአብሔርን የሚቃወም፣ የክብሩንም መገኘት የሚያቃልል ነውና። 9 የፊታቸው ገጽታ ይመሰክርባቸዋል፤ ኀጢአታቸውን እንደ ሰዶም በይፋ ይናገራሉ፤ አይደብቁትምም፤ ጥፋትን በራሳቸው ላይ ስላመጡ፣ ወዮላቸው! 10 ጻድቃን መልካም ነገር እንደሚያገኙ ንገሯቸው፤ የሥራቸውን ፍሬ ይበላሉና። 11 በደለኞች ወዮላቸው! ጥፋት ይመጣባቸዋል! የእጃቸውን ያገኛሉና። 12 ወጣቶች ሕዝቤን ያስጨንቃሉ፤ ሴቶችም ይገዟቸዋል። ሕዝቤ ሆይ፤ መሪዎችህ አሳስተውሃል፤ ከመንገድህም መልሰውሃል። 13 እግዚአብሔር በፍርድ ወንበር ላይ ተቀምጧል፤ በሕዝቡም ላይ ለመፍረድ ተነሥቷል። 14 እግዚአብሔር፣ ከአለቆችና ከሕዝቡ ሽማግሌዎች ጋራ እንዲህ ሲል ይፋረዳል፤ “የወይኔን ቦታ ያጠፋችሁ እናንተ ናችሁ፤ ከድኾች የዘረፋችሁትም በቤታችሁ ይገኛል፤ 15 ሕዝቤን በችግር ስታደቅቁት፣ የድኾችንም ፊት በሐዘን ስታገረጡት ምን ማለታችሁ ነው?” ይላል ጌታ፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር። 16 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “የጽዮን ሴቶች ኰርተዋል፤ ዐንገታቸውን እያሰገጉ፣ በዐይናቸውም እየጠቀሱ ይሄዳሉ፤ እየተቈነኑ በመራመድ፣ የእግራቸውን ዐልቦ ያቃጭላሉ። 17 ስለዚህ፣ ጌታ በጽዮን ሴቶች ዐናት ላይ ቈረቈር ያመጣል፤ እግዚአብሔርም ራሳቸውን ቡሓ ያደርጋል።” 18 በዚያም ቀን ጌታ የክብር ጌጣቸውን ይነጥቃቸዋል፤ የእግር አንባሩን፣ የጠጕር ጌጡን፣ የጨረቃ ቅርጽ ያለውን የዐንገት ጌጥ፣ 19 የጆሮ ጕትቻውን፣ የእጅ አንባሩን፣ የፊት መሸፈኛውን፣ 20 የራስ መሸፈኛውን፣ ዐልቦውን፣ ሻሹን፣ የሽቱ ብልቃጡን፣ አሸንክታቡን፣ 21 የጣት ቀለበቶችንና የአፍንጫ ቀለበቶችን፣ 22 ያማረውን ቀሚስ፣ የውስጥ ልብሱን፣ ካባውን፣ የእጅ ቦርሳውን፣ 23 መስተዋቱን፣ ከጥሩ በፍታ የተሠራውን ልብስ፣ የራስ ጌጡን፣ ዐይነ ርግቡን ሁሉ ይነጥቃቸዋል። 24 በሽቱ ፈንታ ግማት፣ በሻሽ ፈንታ ገመድ፣ አምሮ በተሠራ ጠጕር ፈንታ ቡሓነት፣ ባማረ ልብስ ፈንታ ማቅ፣ በውበትም ፈንታ ጠባሳ ይሆናል። 25 ወንዶቻችሁ በሰይፍ ስለት፣ ተዋጊዎቻችሁ በጦርነት ይወድቃሉ። 26 የጽዮን ደጆች ያዝናሉ፣ ያለቅሳሉም፤ እርሷም ተረስታ በመሬት ላይ ትቀመጣለች። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.