ኢሳይያስ 23 - አዲሱ መደበኛ ትርጒምስለ ጢሮስ የተነገረ ትንቢት 1 ስለ ጢሮስ የተነገረ ንግር፤ የተርሴስ መርከቦች ሆይ፤ ዋይ በሉ! ጢሮስ ተደምስሳለችና፣ ያለ ቤትና ያለ ወደብ ቀርታለች። ከቆጵሮስ ምድር፣ ዜናው ወጥቶላቸዋል። 2 እናንተ የባሕር ተጓዦች ያበለጠጓችሁ፣ በደሴቲቱ የምትኖሩ፣ የሲዶና ነጋዴዎችም ጸጥ በሉ። 3 በታላላቅ ውሆች ላይ፣ ለጢሮስ የሺሖር እህል ይመጣላት ነበር፤ የአባይ መከር ገቢዋ ነበር፤ እርሷም የመንግሥታቱ የንግድ መናኸሪያ ሆነች። 4 አንቺ ሲዶና ሆይ፤ አንቺ የባሕር ምሽግ ሆይ፤ ዕፈሪ፤ ባሕሩ፣ “አላማጥሁም፤ አልወለድሁም፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችን አላሳደግሁም” ብሏልና። 5 ከጢሮስ የሚመጣው ዜና፣ በግብጽ በሚሰማበት ጊዜ ጭንቅ ይይዛቸዋል። 6 እናንተ በደሴቲቱ የምትኖሩ፣ በዋይታ አልቅሱ፤ ወደ ተርሴስም ተሻገሩ፤ 7 እግሮቿ ሩቅ አገር የወሰዷት፣ በዚያም እንድትሰፍር ያደረጓት፣ ጥንታዊቷ የድሮ ከተማ፣ የተድላ ከተማችሁ ይህች ናትን? 8 አክሊል በምታቀዳጀዋ፣ ነጋዴዎቿ መሳፍንት በሆኑ፣ በምድር የከበሩ ሻጮችና ለዋጮች በነበሯት፣ በጢሮስ ላይ ይህን ያሰበ ማን ነበር? 9 የክብርን ሁሉ ትዕቢት ሊያዋርድ፣ በምድር ከፍ ከፍ ያለውንም ሁሉ ዝቅ ሊያደርግ፣ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር ወስኗል። 10 የተርሴስ ልጅ ሆይ፤ ከእንግዲህ የሚከለክልሽ የለምና እንደ አባይ ወንዝ ምድርሽን አጥለቅልቂ። 11 እግዚአብሔር እጁን በባሕር ላይ ዘረጋ፤ መንግሥታቷንም አስደነገጠ፤ የከነዓንም ምሽጎች እንዲፈርሱ፣ ትእዛዝ ሰጠ፤ 12 እንዲህም አለ፤ “አንቺ የተቀጠቀጥሽ የሲዶን ድንግል ሆይ፤ ከእንግዲህ ደስ አይበልሽ! “ተነሺ ወደ ቆጵሮስ ተሻገሪ፤ በዚያም እንኳ ሰላም አታገኚም።” 13 እነሆ፤ የባቢሎናውያንን ምድር ተመልከቱ፤ ሕዝቡ ከንቱ ሆኗል! አሦራውያን የምድረ በዳ አራዊት መፈንጪያ አደረጓት፤ የግንብ ማማቸውን ሠሩባት፤ ምሽጎቿን አወደሙ፤ የፍርስራሽ ክምር አደረጓት። 14 እናንተ የተርሴስ መርከቦች፣ ዋይ በሉ፤ ምሽጋችሁ ፈርሷል! 15 በዚያ ጊዜ ጢሮስ፣ የአንድ ንጉሥ የሕይወት ዘመን ያህል፣ ለሰባ ዓመታት ትረሳለች። ከሰባ ዓመት በኋላ ግን፣ ስለ ጋለሞታዪቱ የተዘፈነው በጢሮስ ላይ ይሆናል፤ 16 “አንች የተረሳሽ ጋለሞታ፤ በገና አንሺ፤ በከተማዪቱ ውስጥ ዙሪ፤ እንድትታወሺም፣ በገናሽን አሳምረሽ ምቺ፤ ብዙ ዘፈን ዝፈኚ።” 17 ሰባው ዓመት ካለፈ በኋላ እግዚአብሔር ጢሮስን ይጐበኛታል፤ ወደ ቀድሞው የግልሙትና ሥራዋ ተመልሳ፣ በምድር ላይ ካሉት የዓለም መንግሥታት ሁሉ ጋራ በንግዷ ትገለሙታለች። 18 ያም ሆኖ ትርፏና ያገኘችው ሁሉ ለእግዚአብሔር የተለየ ይሆናል፤ አይከማችም፤ አይጠራቀምም። ትርፏም በእግዚአብሔር ፊት ለሚኖሩት የተትረፈረፈ ምግብና ጥሩ ልብስ ይሆናል። |
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.
Biblica, Inc.